ልዩልዩ
ለወንድ ልጅ መጸ’ነስ ምክንያት የሆነው የዋይ ክሮሞዞም በመጥፋት ላይ መሆኑን ሳይንቲስቶች ተናገሩ
ለዚህ ክሮሞዞም ምትክ ካልተገኘ ወንድ የሚባል ፍጡር ከምድረገጽ ሊጠፋ ይችል ይሆን?
የወንድነት ጾታን የሚወስን አዲስ ክሮሞዞም መፈጠሩም ተነግሯል
ለወንድ ልጅ መጸ’ነስ ምክንያት የሆነው የዋይ ክሮሞዞም በመጥፋት ላይ መሆኑን ሳይንቲስቶች ተናገሩ፡፡
ተመራማሪዎች ከፍጡራን መካከል ሰፊውን ምርምር ለሰው ልጅ የሰጡ ሲሆን ያልተመረመረ የሰው ልጅ አካል ወይም ህይወት የለም ማለት ይቻላል፡፡
በተለይም የሰው ልጅ ስነ ህይወታዊ ባህሪያት ከነዚህ መካከል ዋነኛው ሲሆን ለጾታዊ አፈጣጠር ዋነኛ መሰረት የሆኑት የሴትነት ወይም ወንድነት ጾታ ምክንያት የሚባሉት የኤክስ እና ዋይ ክሮሞዞም ወይም ሀብለብራሂ ይጠቀሳሉ፡፡
ለጽንስ መፈጠር መነሻ የሆኑት ሁለቱ ወላጆች ማለትም የሴቷ ኤክስ የወንዱ ወይም የአባትየው ደግሞ ዋይ ወይም ኤክስ ክሮሞዞም እንደሆኑ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡
በሁለቱ ወገኖች ግንኙነት የሚፈጠረውን ጽንስ ጾታ የሚወስኑት እነዚህ ሁለት ክሮሞዞሞች ሲሆኑ ለወንድ ልጅ መጸነስ ምክንያት የሆነው የዋይ ክሮሞዞም የሚገኘው ከወንዱ አልያም ከአባትየው ነው።
የጃፓን ሳይንቲስቶች እንዳረጋገጡት ለወንድ ልጅ መጸ’ነስ ምክንያት የሆነው ይህ የዋይ ክሮሞዞም በመቀነስ ላይ ይገኛል።
የጃፓን ሳይንስ አካዳሚ ተመራማሪዎች በአይጦች ላይ ባደረጉት ምርምር የዋይ ክሮሞዞም ቁጥር የቀነሰ ሲሆን ከአይጥ ውጪ ባሉ አጥቢ እንስሳት ላይ በተደረገ
ተመሳሳይ ምርምር ተመሳሳይ ውጤት ማሳየቱን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ምርምር መሰረት የዋይ ክሮሞዞም ከ10 ሚሊዮን ዓመት በኋላ ሊጠፋ እንደሚችል ተመራማሪዎቹ አመልክተዋል ተብሏል፡፡
በጃፓኗ አማሚ ኦሺማ ደሴት በሚኖሩ ሴትና ወንድ አይጦች ላይ በተደረገው ምርምር የሁለቱም ጾታ አይጦች የኤክስ ክሮሞዞም ብቻ እንዳላቸው መረጋገጡ ተገልጿል፡፡
ይሁንና የወንድ ጾታን የሚወስነው የዋይ ክሮሞዞም ቢጠፋም ወይም ቁጥሩ እየቀነሰ ቢመጣም የወንድነት ጾታን የሚወስን አዲስ ክሮሞዞም መፈጠሩን ሳይንቲስቶች ተናግረዋል፡፡
የአውስትራሊያ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዋ ጄኒ ግሬቭስ በበኩላቸው የዋይ ክሮሞዞም ከ10 ሚሊዮን ዓመት በኋላ እንደሚጠፋ ነገር ግን ዋይ ክሮሞዞምን የሚተካ አዲስ አልያም ጾታን የሚወስን አዲስ ክሮሞዞም ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡