ወንዶችና ሴቶች የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩባት የናይጄሪያዋ ‘ኡባንግ’ መንደር
ወንዶችና ሴቶች በጋራ የሚጠቀሙባቸው ቃላቶች ቢኖሩም፤ ጾታ ላይ በመመስረት የአነጋገር ዘይቤና የቃላት ልዩነቶችም አሉ
ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በየራሳቸው ቋንቋ እየተነጋገሩ ያለምንም ችግር መግባባት እንደሚችሉም ይነገራል
“ሴቶች ከቬነስ ወንዶች ደግሞ ከማርስ መምጣታቸውን ለማረጋገጥ ከኡባንግ ውጪ ሌላ ስፍራ የለም” ይላሉ ወንዶችና ሴቶች የተለያዩ ቋንቋ የሚናገሩባት የናይጄሪያዋ ልዩ የገጠራማ አካባቢ ነዋሪዎች።
በአንድ አካባቢ አብረው ያደጉ ወንድና ሴት ካደጉ በኋላ የተለያዩ ቋንቋን ይናገራሉ የሚለውን ማመን ቢከብድም፤ በኡባንግ ነዋሪዎች ዘንድ ግን ይህ እውነት ይላል ለየት ያሉ የዓለማችንን ክስተቶች በመዘገብ የሚታወቀው ኦዲቲ ሴንተራል ቢቢሲን ጠቅሶ ባወጣው መረጃ።
ሁለቱም ጾታዎች የሚናገሩት ቋንቋ የተለያየ መሆኑን የሚያሳይ በቂ የሆኑ ምሳሌዎች አሉ የተባለ ሲሆን፤ ለምሳሌ ልብስ ‘clothing’ የሚለውን ለመግለጽ ወንዶች ‘nki’, የሚል ቃል ሲጠቀሙ፤ ሴቶች ደግሞ ‘ariga’ የሚል ቃል ይጠቀማሉ፤ ዛፍ (tree) ለመግለፅም ወንዶች ‘kitchi’ የሚል ቃል ሲጠቀሙ፤ ሴቶች ደጎም ‘okweng’ ይላሉ።
ሁለቱም ጾታዎች የሚናገሩት ቋንቋ ጋር የአነጋገር ዘይቤ ልዩነቶች አሉ የተባለ ሲሆን፤ አንድን ነገር ለመግለጽ ሙሉ በሙሉ የተለያዩ ቃላትን ሲጠቀሙም ይስተዋላል።
አንትሮፖሎጂስቷ ቺ ቺ አንዲ እንደሚናገሩት፤ “ወንዶችና ሴቶች በጋራ የሚጠቀሙባቸው ቃላቶች ቢኖሩም፤ ጾታ ላይ በመመስረት ሙሉ በሙሉ የሚለያዩ ቃላትም አሉ፤ የአነጋገር ዘይቤያቸው እና ፊደሎቻቸውም ሙሉ በሙሉ የተለያዩ ናቸው።”
በጣም የሚያስገርመው ነገር ግን ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በየራሳቸው ቋንቋ እየተነጋገሩ እርስ በርሳቸው የሚሉትን ነገር ያለምን ችግር መረዳት ይችላሉ ብለዋል።
ወንዶችና ሴቶች በቤተሰቦቻው ውስጥ በጋራ ሆነው ሁለቱን ቋንቋ እየተናገሩ የሚያድጉ ሲሆን፤ ልክ 10 ዓመት ሲሞላቸው ወንዶች የራሳቸውን ቋንቋ እንዲናገሩ ይጠበቅባቸዋል።
ወንዶቹ እድሜያቸው 10 ዓመት ሲሞላው የራሳቸውን ቋንቋ እንዲናገሩ የሚነግራቸው የለም፤ በራሳቸው ነው ወደ ወንዶች ቋንቋ ቀይረው የሚናገሩት የተባለ ሲሆን፤ ይህ ሲሆን እየበሰለ ስለመሄዱ ማረጋገጫ መሆኑንም የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የናይጄሪያዋ ኡባንግ ነዋሪዎች የሆኑ ወንዶችና ሴቶች እንዴት የተለያየ ቋንቋ መናገር ጀመሩ ለሚለው እስካሁን መልስ ያልተገኘለት ጉዳይ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ሀይማኖታዊ ትርጉም ሲሰጡት ይሰማሉ።
እንደ ኡባንግ ነዋሪዎች ገለጻ፤ “ፈጣሪ አዳም እና ሄዋንን ከፈጠረ በኋላ ልክ እንደ ኡባንግ ሰዎች የተለያየ ቋንቋ ሰጣቸው፤ በዚህም ለሁሉም ብሄሮች ሁለት ሁለት ቋንቋ ለመስጠት አቅዶ ነበር፤ ነገር ግን በምድር ላይ በቂ ቋንቋ በማጣቱ፤ ስራዉን ኡባንግ ላይ አቆመ” ይላሉ።
አሁን አሁን በናይጄሪያ ወጣቶች ዘንድ እንግሊዝኛ መናገር በስፋት እየተለመደ መምጣቱን ተከትሎ የኡባንግ የሁለት ቋንቋ መጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ተብሏል።