በቀጣዮቹ 50 ዓመታት ውስጥ የጣልያን ህዝብ ብዛት በ12 ሚሊዮን ይቀንሳል ተብሏል
የጣልያን ህዝብ ብዛት በወሊድ ምጣኔ መቀነስ እየተፈተነ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ጣልያን በአውሮፓ ከሩሲያ ፣ጀርመን፣ ብሪታንያ እና ከፈረንሳይ በመቀጠል አምስተኛዋ ብዙ የህዝብ ብዛት ያላት ሀገር ስትሆን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግን የዓመታዊ የውልደት መጠኗ እየቀነሰ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
እንደ ሀገሪቱ የስታስቲክስ ተቋም ጥናት ከሆነ የጣልያን የውልደት መጠን በዚሁ ከቀጠለ ከ50 ዓመት በኋላ የህዝብ ብዛቷ አሁን ካለበት 60 ሚሊዮን ወደ 47 ሚሊዮን ያሽቆለቁላል፡፡
አሁን ባለው የውልደት መጠን ከቀጠለ በአጠቃላይ ጣልያን የ12 ሚሊዮን ገደማ ህዝቧን እንደምታጣ የተገለጸ ሲሆን ዜጎች የውልደት መጠናቸውን ሊያሻሽሉ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ለውልደት መጠኑ መቀነስ በእድሜ የገፉ ዜጎች ቁጥር መጨመር፣ የኑሮ መወደድ እና የአየር ንብረት ለውጥ ለጣልያን ህዝብ ቁጥር መቀነስ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሁን ያለው ዓመታዊ የውልደት መጠን ከቀጠለ የጣልያን ህዝብ ብዛት በ2050 ወደ 54 ሚሊዮን በ2070 ደግሞ ወደ 47 ሚሊዮን ዝቅ ሊል እንደሚችል ተገምቷል፡፡
እንዲሁም ከላይ በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሚሆኑ ዜጎች ቁጥር ከጠቅላላ ህዝቡ የ34 በመቶ እና የ50 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋልም ተብሏል፡፡
በጣልያን በፈረንጆቹ 2021 ዓመት 400 ሺህ ገደማ ህጻናት የተወለዱ ሲሆን 709 ሺህ ዜጎች ደግሞ ህይወታቸው ማለፉን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
በአውሮፓ ሩሲያ 145 ሚሊዮን፣ ጀርመን 83 ሚሊዮን፣ ብሪታንያ 68 ሚሊዮን፣ ፈረንሳይ 65 ሚሊዮን የህዝብ ብዛት ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡