የቀድሞው የሱዳን ፕሬዘዳንት አልበሽር ለዓለምአቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፈው እንዲሰጡ ተወሰነ
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዘዳንት አልበሽር ለዓለምአቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፈው እንዲሰጡ ተወሰነ
የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት አባል የሆኑት ሞሃመድ ሀሰን አልታይሺ ከስልጣን የተባረሩትን የቀድሞውን የሀገሪቱን መሪ፣ ፕሬዘዳንት ኦማር አልበሽርንና ሌሎች ተፈላጊዎችን ለአለምአቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፎ ለመስጠት ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
አልታይሺ ይህን ያስታወቁት የሱዳን መንግስት ቃል አቀባይ በመሆን ከ “ዳርፉር ፓዝ ኦን ዘሪቮሉሽናሪ ፍሮንት” ጋር በጁባ ካካሄዱት ድርድር በኋላ ነው፡፡
“የቀድሞው ፕሬዘዳንት አልበሽርና ሌሎች ተፈላጊዎች ተላልፈው እንዲሰጡ የተወሰነው፣ ፍትህን ከማስፈንና ጥፋት መታለፍ የለበትም ከሚል እምነት ነው” በማለት የዉሳኔውን ትክክለኛነት አልታይሺ አብራርተዋል፡፡
አልታይሺ “ፍትህ የሚረጋገጠው የችግሩን ስር በመፍታትና የችግሩን ሰለባዎች በመካስ ነው፡፡ በዳርፍር የጦር ወንጀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት ተካሂዷል፤ ስለዚህ የእስር ማዘዧ የወጣባቸውን ሁሉንም ተፈላጊዎች ለአለምአቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድቤት ተላልፈው እንዲሰጡ ተስማምተናል” ብለዋል፡፡
በዳርፉር ለተፈጸሙ ወንጀሎች ልዩ ፍርድ ቤት ለማቋቋም መስማማታቸውን የገለጹት አልታይሺ በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ እንመክራለን ብለዋል፡፡
“ፍትህን ማስፈን የታህሳሱ አብዮት ጥያቄ ነበር፤ ከዚህ ወጭ ሰላም አይኖርም”
ከስልጣን የተነሱት ኦማር አልበሽርና ሌሎች 51 ሰዎች ምእራባዊ ዳርፉር ግዛት ውስጥ ፈጸሙት በተባለ የጦር ወንጀል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ በ2008 እና በ2009 የእስር ማዘዣ አውጥቶባቸው ነበር፡፡
አልበሽር ገንዘብ ከውጭ ምንጮች ከመቀበል ባሻገር ብዙ የወንጀል ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት የሱዳኑ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ታጅ አልሰር አልኢንክር የአልበሽር ለዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፎ መሰጠት በድርድሩ፣ በተጎጂዎችና በተጎጂ ቤተሰቦች እንደሚወሰን ገልጸው ነበር፡፡
አልኢንክር ይህን ያሉት በአልበሽር ተላልፎ መሰጠት ጉዳይ ላይ ጥያቄ ላቀረቡት ከአሜሪካ ኮንግረስ ለመጡ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን አባለት ነበር፡፡