ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የድንበር ውዝግብ ለማሳወቅ ጎረቤት ሀገራትን እየዞረች ነው
አምባ. ዲና “ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ማጉላት ያልፈለገችው ጉዳዩን ቀጠናዊ ላለማድረግ ነው” ማለታቸው ይታወሳል
የሱዳን የተለያዩ ባለስልጣናት ሳዑዲን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ሀገራት ጉዳዩን ለማሳወቅ አቅንተዋል
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤትና የሚኒስትሮች የጋራ ምክር ቤት ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የድንበር ውዝግብ በተመለከተ ወደ ጎረቤት ሀገራት ጉብኝት እንዲደረግ መወሰኑን አስታወቀ፡፡
የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ወደ ካይሮ፣አስመራ፣ጁባና ሳዑዲ አረቢያ በመሄድ ጉዳዩን እያስረዱ ነው ተብሏል፡፡ በዚህም መሰረት የሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤቱ አባል ሌፍተናንት ጄነራል ሻምሰዲን ካባሺ በደቡብ ሱዳን፣ የሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ሌፍተናንት ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወደ ኤርትራ፣ የሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤቱ አባል ሌፍተናንት ጄነራል ኢብራሂም ጃቢር ወደ ቻድ፣ መሐመድ ፋኪ ሱሌማን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
የሀገሪቱ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ቀመረዲን፣ የስለላ ኃላፊው ጄነራል ጃማል አዲን ኦማር ፣የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ፋይሳል መሐመድ ሳሊህ እና የሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤቱ አባል ሌፍተናንት ጄነራል ሻምስ ኢል ዲን ካባሺ ዛሬ ወደ ካይሮ አቅንተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ማክስኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ማጉላት ያልፈለገችው ጉዳዩን ቀጠናዊ ላለማድረግ ነው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን ሱዳን ግን ባለሥልጣኖቿን ወደ ተለያዩ ሀገራት መላኳን ቀጥላለች፡፡
“በጉዳዩ ላይ ሱዳንን የሚገፉ ሌሎች ከጀርባ ያሉ አካላት ስላሉ የነሱን ካርድ ላለመጫወት ነበር ዝም ያልነው ፣ ይህ ግን እንደፍርሀትና እንደመወላወል መቆጠር የለበትም” ሲሉ አምባደር ዲና መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በትናንትናው ዕለት ድንበር አካባቢ ከሀገሪቱ ጦር ጋር ቆይታ ያደረጉት የሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤቱ ሊቀመንበር ሌፍተናንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ፣ “ከጀርባችን ማንም የለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሌፍተናንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ለሀገሪቱ መከለከያ ሰራዊት አመራሮችና አባላት መመሪያ መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡ ሊቀመንበሩ በድንበር አካባቢ ባደረጉት ጉብኝት ቦታው የሱዳን በመሆኑ ከዚህ ስፍራ አንወጣም ማለታቸውን የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
የሱዳን ጦር ድንበር ጥሶ የኢትዮጵያን ግዛት መቆጣጠሩን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት ፣ ሱዳን ከሰላማዊ መንገድ ውጭ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንድታቆም በተደጋጋሚ ጠይቋል፡፡ በድንበር ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዲቻል ሱዳን የ1972ቱን (እ.ኤ.አ) ስምምነት እንድታከብር እና ከያዘችው መሬት ወጥታ ወደ ቀድሞ ስፍራዋ እንድትመለስ ኢትዮጵያ አሳስባለች፡፡ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጀመሯን ተከትሎ በተፈጠረው ክፍተት ፣ ዘመቻው ከተጀመረ ከ 6 ቀናት በኋላ ሱዳን በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቃ መግባቷን የኢትዮጵያ መንግስት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ በዚህም የንጹሃን ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በርካታ ንብረትም ወድሟል ነው የተባለው፡፡