ሱዳን የድንበሩን ውጥረት ሊያባብስ በሚችል መልኩ የኢትዮጵያ የጦር ጀት ድንበር ጥሶ ገብቷል ስትል ከሰሰች
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊትር ገጹ እንደጻፈው "የኢትዮጵያ የጦር ጀት የሱዳንን ድንበር ጥሶ ገብቷል፤ይህም አደገኛ ዉጤት ሊያስከትል የሚችልና በድንበር አካባቢ ያለውን ውጥረት የሚያባብስ ነው" ብሏል፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ሁኔታ የማባባስ" ያለውን ድርጊት እንደሚያወግዝና በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ግንኙነትና በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ላይ አደገኛ የሆነ ውጤት ስለሚያስከትል ይህ “ትንኮሳ” መደገም የለበትም ብሏል፡፡
ሱዳን በአሁን ወቅት የያዘችው ቦታ "በታሪክ የሱዳን አካል መሆኑን" የሱዳን የድንበር ኮሚቴ ሊቀመንበር አስታውቀዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ዛሬ በሱዳን ለሚገኙ የዲፕሎመቲክ ማህበረሰብ አባላት በሰጡት መግለጫ “የሱዳን ወታደር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አልገባም ይልቁንም የሱዳን የነበረ ቦታን ነው የተቆጣጠረው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ነገርግን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት በሰጡት መግለጫ “የሱዳን ኃይል በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የመግፋት እና ወደ ውስጥ ዘልቆ የመግባት እንቅስቃሴ እያሳየ ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
አምባሳደር ዲና ሱዳን ድንበር ጥሳ መግባቷንና ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ኢትጵዮጵያ እንደምትፈልግና ለጦርነት እንደማትቸኩልም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር መጣሷንና ይህን ያደረገችው ጦሩ በትግራይ ክልል በህግ ማስከበር ዘመቻ መሰማራቱን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት በማየት መሆኑን ገልጿል፡፡