“ሱዳን ከአሁን በኋላ በድርድሩ ሂደት የራሷ አጀንዳ የላትም”- አምባሳደር ዲና
ይህን የሚደርጉት “አፍሪካ እንዳይሳካላት፤ ችግሩ በአፍሪካ እንዳይፈታ” ለማድረግ በማሰብ ጭምር እንደሆነም ገልጸዋል
“ድርድሩ ሌሎች አካላትን ያካት ማለት በአፍሪካ እምነት እንደሌላቸው ማሳያ” እንደሆነም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል
እነ ግብጽ በግድቡ የድርድር ሂደት “ከአፍሪካ ህብረት ውጭ ሌሎች አካላት ይካተቱ” ማለታቸው “ለአፍሪካ አክብሮትም ሆነ በአፍሪካ እምነት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ዲና ይህን ያሉት ሳምንታዊ መግለጫን በሰጡበት በዛሬው ዕለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ “ችግሩን በአፍሪካዊ ማዕቀፍ እንፍታ ማለቷ አስራ አንዱም የተፋሰሱ ሃገራት አፍሪካዊ በመሆናቸው፣ ወንዙም አፍሪካዊ በመሆኑ እና የሚፈሰው በአፍሪካ በመሆኑ ነው” ያሉት አምባሳደር ዲና በግብጽ እና ሱዳን በኩል “ከዚህ ማዕቀፍ የማውጣት” ፍላጎት እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ይህ ከአፍሪካዊ ማዕቀፍ የመውጣት ፍላጎት “[ግብጽ] የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በነበረችበት ጊዜ፣ ደቡብ አፍሪካ ሊቀመንበር ሆናም ሳለ የነበረ ነው”ያሉም ሲሆን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሊቀመንበር ሆና ህብረቱን በምትመራበት በዚህ ወቅት ጭምር ፍላጎቱ እንዳለም ገልጸዋል፡፡
ሌሎች የውጪ አካላት ተካተው “ድርድሩ የአራትዮሽ (ኳርቴት)” እንዲሆን ብቻም ሳይሆን ይጨመሩ የሚሏቸው የውጭ አካላት “ከህብረቱ እኩል የማደራደር ሚና ይኑራቸው” በሚል እየጠየቁ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት፡፡
ይህ “አፍሪካ እንዳይሳካላት፤ ችግሩ በአፍሪካ እንዳይፈታ” ለማድረግ ነው ሲሉም አስቀምጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ “በሙሌቱ እና በአስተዳደሩ እንነጋገር” ማለቷን የገለጹት አምባሳደር ዲና “ሱዳን ከአሁን በኋላ በድርድሩ ሂደት የራሷ አጀንዳ የላትም” ብለዋል፤ ከመረጃ ጋር የተያዙ እና ሌሎች ጥያቄዎቿ መመለሳቸውን በመጠቆም፡፡
“የግድቡን ደህንነት፣ አሞላል በተመለከተ ካስፈለገ እንፈርምላችኋለን ጭምር ብለናቸዋል” ነው ቃል አቀባዩ ያሉት፡፡
ከዚህ በኋላ ሱዳን “በውክልና እንጂ ይዛ የምትቀጥለው የራሷ አጀንዳ” እንደሌለም ገልጸዋል፡፡
“በተለይ ወታደራዊ ክንፉ የሌሎችን ተልዕኮና መልዕክት ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል”ም ነው አምባሳደር ዲና ያሉት፡፡
“ከኢትዮጵያ በላይ ግድቡ እነሱን እንደሚጠቅም” ቀደም ሲል መረዳታቸውን ገልጸው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡