ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ግድቡን “የአረብ ሃገራት የውሃ ደህንነት ስጋት” አድርገው ማቅረባቸው “ተቀባይነት” እንደሌለው አሳሰበች
ከኪንሻሳው የግድቡ ስብሰባ ጋር በተያያዘ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ አምባሳደሮች ገለጻ ተደርጓል
“ለፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል የሚያራምዱት አቋም ተቀባይነት የሌለውና ሁሉም በአጽንኦት ሊገነዘበው የሚገባ” እንደሆነም ነው ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ያሳሰቡት
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሳምንት ( እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 4 እና 5 ቀን 2021) በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ከተካሄደው ህዳሴ ግድቡን የተመለከተ ስብሰባ ጋር በተያያዘ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ አምባሳደሮች ገለጻ አደረገች፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ስር ስለተካሄደው የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች የሶስትዮሽ ስብሰባ ገለጻ የተደረገው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና በውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ነው፡፡
በገለጻው በስብሰባው ውይይት የተደረገባቸውን ጉዳዮች እና የኢትዮጵያን ዕይታ በተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ ድርድሩ በህብረቱ ጥላ ስር እንዲቀጥል ያላትን ጽኑ እምነት ለአምባሳደሮቹ መገለጹንም ነው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው፡፡
ሶስቱ ሀገራት የአባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ያላቸው አማራጭ በትብብር እና በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ስሜት በጋራ መስራት እንደሆነ ኢትዮጵያ ደጋግማ ገልጻለች፡፡
ይህንንም ሚኒስትሮቹ ለአምባሳደሮቹ አስረድተዋል።
በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ቢሮ ስብሰባ በተደረገበት ባሳለፍነው ዓመት ሃምሌ በ2012 ዓ/ም ላይ ድርድሩን ስኬታማ ለማድረግ እና መተማመንን ለማጎልበት መግባባት ላይ ተደርሶ መግለጫ ጭምር መውጣቱን ያስታወሰው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በቅድሚያ በግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት እና ተያያዥ የውሃ አለቃቀቅ ጉዳዮች በመቀጠልም ሁሉን አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ስምምነት ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ገልጻለች ብሏል።
የመረጃ ልውውጥ የማድረጉን ተነሳሽነት በቅን ልቦና በመውሰድ ኢትዮጵያ በቀጣዩ ሐምሌ ወር የሚደረገውን የ2ኛ ዓመት ሙሌት አስመልከቶ በውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሯ በኩል ለግብጽ እና ሱዳን ደብዳቤ መላኳንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።
ሆኖም ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ በደብዳቤው ለመረጃ ልውውጡ የሚሆን ተወካይ እንዲመድቡ ያቀረበችውን ጥያቄ አልተቀበሉትም፡፡
“ሁሉም የአባይ ተፋሰስ ሃገራት አፍሪካዊ ሆነው ሳለ ግብጽና ሱዳን ግድቡ የአረብ ሃገራትን አደጋ ላይ የሚጥል የውሃ ደህንነት ስጋት አድርገው ማቅረባቸው የሚያሳዝን” እንደሆነ የገለጹት የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) “ለፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል የሚያራምዱት አቋም ተቀባይነት የሌለውና ሁሉም በአጽንኦት ሊገነዘበው የሚገባ” እንደሆነ አሳስበዋል።
ከግድቡ ወቅታዊ የድርድር ሁኔታ በዘለለ ለአምባሳደሮቹ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተም ገለጻ ተደርጓል፡፡
በገለጻው ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተደረጉ ስምምነቶች እና ባሉት የድንበር አሰራር ማዕቀፎች አማካኝነት በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኗ ተገልጿል።
አምባሳደሮቹ በበኩላቸው የግድቡ የድርድር ጉዳይ በሕብረቱ ማዕቀፍ ስር “አፍሪካዊ መፍትሔ፣ ለአፍሪካ ችግር” በሚለው መርህ መሰረት ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሃገራቱ በዚሁ ማዕቀፍ ድርድራቸውን እንዲቀጥሉም አበረታተዋል።
የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቹን ለመፍታት የወሰደችውን አቋም “ማድነቃቸውን” ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።