ሱዳን ከያዘችው ግዛት እንድትወጣ በኢትዮጵያ የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ እንደማትቀበል ገለጸች
የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር “ገና ያላስመለስነው ቦታ አለ” ብለዋል
ሱዳን በትግራይ የነበረውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ ከያዘችው ቦታ እንድትለቅ ኢትዮጵያ መጠየቋ ይታወሳል
የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር ሌተናንት ጄኔራል ያሲን ኢብራሂም ከአል አራቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣ የህዳሴ ግድብ እና የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ድርድር ለመጓተቱ አዲስ አበባን ተጠያቂ በማድረግ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ይህ የሚኒስትሩ ውንጀላ በኢትዮጵያ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም ባለፈ ጉዳዩን ኢትዮጵያ በተቃራኒው ነው የምትገልጸው፡፡ ከግድቡ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜያት ሱዳን እና ግብፅ የተለያየ አቋም የማራመድ እና ወደ ድርድሩም ወጣ ገባ የማለት አዝማሚያ እንደሚያሳዩ በኢትዮጵያ በኩል ይገለጻል፡፡ ይህም ለድርድሩ መዘግየት እና ስምምነት ላይ ላለመደረሱ ምክንያት መሆኑን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ጉዳይም ቢሆን ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የተደረሱ ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ በውይይት እንዲፈታ ያላትን አቋም በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡ ይሁን እንጂ ድርድሮች እየተካሔዱ ባሉበት ሁኔታ ፣ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ እያለች ክፍተቱን በመጠቀም ሱዳን ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ ማዝመቷን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ “የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ፣ የኢትዮጵያ ጦር ተዳክሟል በሚል ግምት ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ጦሯን ስለማዝመቷ” ከአል አረቢያ ጋዜጠኛ ለሚኒስትሩ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ፣ “ወደ ድንበር ጦራችንን ያስጠጋነው ከኢትዮጵያ መንግስት በቀረበልን ጥያቄ ነው” ካሉ በኋላ በዚያውም “በኢትዮጵያ ተይዞብናል” የሚሉትን ይዞታ ለማስመለስ ወደ ውስጥ ዘልቀው መግባታቸውን የሱዳን መከላከያ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
አምባሳደር ዲና በባለፈው ሳምንት መግለጫቸው “ኢትዮጵያ ድንበሩን አሳልፎ የሚሰጥ መሪ የላትም” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ሱዳን ከቀድሞው ይዞታዋ አልፋ ከገባችበት ጦሯን እንድታስወጣ እና ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር “ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ አንቀበልም” ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ያሲን ኢብራሂም ፣ ይባስ ብለው ፣ “ኢትዮጵያ መልቀቅ ያለባት ገና ያላስመለሱት ይዞታ” መኖሩን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይነት ጦርነት ስለመቀጠል ያላቸውን ሀሳብ በተመለከተ ሲጠየቁ “ከያዝነው ቦታ አንወጣም ፤ ይዞታችንን እንደያዝን በድርድር መፍታት እንፈልጋለን” ካሉ በኋላ “ይህ ካልሆነ ነው ወደ ቀጣይ እርምጃ ልንሄድ የምንችለው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከጀመረች ከ6 ቀናት በኋላ ፣ ከጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ፣ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ወረራ መጀመሯን ኢትዮጵያ አስታውቃለች፡፡ በዚህም የንጹሃን ህይወት ሲያልፍ በስፍራው የነበሩ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች በርካታ ንብረት መውደሙን እና መዘረፉንም የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ አድርጓል፡፡ ይህን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡