የሱዳን ወረራ አሁን ላለው የድንበር ውጥረት መንስዔ ስለመሆኑ አቶ ደመቀ ለብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብራሩ
የኢትዮጵያ ም/ጠ/ሚ እና ውጭ ጉ/ሚ ደመቀ መኮንን ብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያይተዋል
በሱዳን የሽግግር አስተዳደር የወታደራዊው ክንፍ መሪዎች ራሳቸውን ብቸኛ የሀገሪቱ ታዳጊ ማስመሰል እንደሚፈልጉ ተንታኞች ይገልጻሉ
የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ የሱዳን ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ጥር 14 ቀነን 2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡
ዶሚኒክ ራብ ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር ከተገናኙ በኋላ ፣ አመሻሽ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሁለቱ አካላት በነበራቸው ውይይት አቶ ደመቀ ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውጥረት በተመለከተ ፣ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ በነበረችበት ወቅት ሱዳን ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባቷን አስረድተዋል፡፡
ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት ፣ ምንም እንኳን ሱዳን ለጦርነት ብትዘጋጀም ኢትዮጵያ አሁንም የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ በውይይት የመፍታት አቋም እንዳላት ለብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የሕዳሴ ግድቡን ድርድር በተመለከተ ግብፅ እና ሱዳን ወጣ ገባ የማለት አዝማሚያ እንደሚያሳዩ እና ኢትዮጵያ ሁሉም ሀገራት ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን አማራጭ በማንጸባረቅ በወጥ አቋም እንደምትደራደር አቶ ደመቀ ገልጸውላቸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ዶሚኒክ ራብ ከሱዳን የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውጥረት በውይት እንዲፈታ ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል፡፡
ዶሚኒክ ራብ በካርቱም ቆይታቸው በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበርና በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ፣ ከሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክና ከካቢኔ አባሎቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በተደጋጋሚ “የራሳችንን ግዛት ነው የያዝነው እንጂ የኢትዮጵያን ድንበር አልፈን አልሔድንም የሚሉት ሌ/ጄኔራል አል ቡርሃን ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት አንፈልግም ፤ ነገር ግን አንድ ኢንች እንኳን መሬታችንን አሳልፈን አንሰጥም" ብለዋል፡፡ ከብሪታንያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ውይይትም ይህንኑ ማስረዳታቸውን የሱዳን ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
በሱዳን የሽግግር አስተዳደር ወታደራዊው ክንፍ ራሱን ብቸኛ የሀገሪቱ ታዳጊ አድርጎ ለሀገሪቱ ህዝብ ለማሳየት ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎትን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ተንታኞች ያብራራሉ፡፡
በሱዳን የፖለቲካ ተንታኝ የሆነችው ራሻ አዋድ ፣ የሀገሪቱ ጦር ውጊያ ውስጥ የመግባት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ትገልጻለች፡፡ ተንታኟን በመጥቀስ ዘ ናሺናል እንደዘገበው አል ቡርሃን የሚመሩት የሀገሪቱ ጦር ሱዳንን የመጠበቅ እና ፍላጎቷን የማሳካት ብቸኛው ኃይል እርሱ መሆኑን ለህዝቡ ማሳወቅ ይፈልጋል፡፡
በተቃራኒው በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የሚመራው ሲቪሉ የመንግስት ክንፍ ፣ ሀገሪቱ በሽግግር ላይ ባለችበት እና በኢኮኖሚ ቀውስ እየተፈተነች በምትገኝበት በዚህ ወቅት ፣ ምንም አይነት ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ተንታኟ ገልጻለች፡፡ የሽግግሩን መንግስት የሚመሩት ሁለቱ አካላት በህዝቡ ተቀባይነትን ለማግኘት የሚሄዱባቸው የተለያዩ መንገዶች አለመግባባት እንዳለባቸው የሚያሳዩ መሆኑንም ነው የጠቆመችው፡፡
በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ ከሳምንት በኋላ እንደአዲስ ያገረሸው የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ውዝግብ ሀገራቱ ከረዥም አመታት በኋላ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡