“የሱዳን ኃይል በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ገፍቶ የመግባት እንቅስቃሴ ላይ ነው” አምባ. ዲና ሙፍቲ
አምባሳደር ዲና “የኢትዮጵያ መለሳለስ እንደፍርሀትና መቆጠር የለበትም” ብለዋል
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን ችግር ማጉላት ያልፈለገችው ጉዳዩን ቀጠናዊ ላለማድረግ እንደነበር ቃል አቀባዩ ገልጸዋል
የኢትዮጵያ እና የሱዳን የድንበር ውዝግብ ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ውጥረት ላይ መድረሱ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ “የሱዳን ኃይል በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የመግፋት እና ወደ ውስጥ ዘልቆ የመግባት እንቅስቃሴ እያሳየ ነው ያለው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ ድርጊት እንደማያዋጣ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየገለጸች እንደምትገኝም ነው አምባሳደሩ የገለጹት፡፡
ድንበሩ እስኪካለል ድረስ ነባራዊው ሁኔታ ባለበት እንዲቆይ (ሁለቱም ሀገራት በነበሩበት እንዲቆዩ) እ.ኤ.አ በ 1972 ስምምነት ተደርሶ እንደነበር ያነሱት ቃል አቀባዩ ፣ የአሁኑ የሱዳን ድርጊት ይህን ስምምነት የሚጥስ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና እንዳሉት ፣ ሱዳን ጦሯን አሰልፋ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግፋት የጀመረችው ፣ በድንበር አካባቢ የሳሳ የመከላከያና የጸጥታ ሁኔታ ስላለ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰጡት መግለጫ ፣ ከጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ሱዳን በድንበር አካባቢ ጦሯን አሰልፋ ጥቃት መፈጸም መጀመሯን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ማለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ዘመቻ ከጀመረ ከ 6 ቀናት በኋላ ነው ሱዳን ወረራ የጀመረችው፡፡
“ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ማጉላት ያልፈለገችው ጉዳዩን ቀጠናዊ ላለማድረግ ነበር” ያሉት አምባሳደር ዲና “ነገር ግን ይህ ገደብ አለው” ብለዋል።
“በጉዳዩ ላይ ሱዳንን የሚገፉ ሌሎች ከጀርባ ያሉ አካላት ስላሉ የነሱን ካርድ ላለመጫወት ነበር ዝም ያልነው ፣ ይህ ግን እንደፍርሀትና እንደመወላወል መቆጠር የለበትም” ሲሉም ተናግረዋል።
“ስለዲፕሎማሲ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ የሚያውቅ የለም” በማለት አሁንም ችግሩን በውይይት ለመፍታት ሱዳን ዝግጁ መሆን እንዳለባት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አሳስበዋል።
“ኢትዮጵያ ጦርነት ትጀምራለች ወይ?” ተብለው የተጠየቁት ቃል አቀባዩ “ጦርነት አያስቸኩልም፣ አፍንጫህን የመታህን ወዲያውኑ አፍንጫውን ላትመታው ትችላለህ ፤ ሌላ ጊዜ ግን አንገቱንም ልትቆርጠው ትችላለህ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።