ከወሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሞት ጋር በተያያዘ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሏል
በወሎ ዩኒቨርሲቲ አንድ ተማሪ ተመትቶ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን፣የድርጊቱን ሁኔታና የፈጻሚዎቹን ማንነት ለማወቅ ትናንት “ቀኑን ሙሉ እና አምሽተንም ጭምር ጥረት ስናደርግ” ነበር ብለዋል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን፡፡
ዶ/ር አባተ ጌታሁን አንድ ተጠርጣሪ ትናንት ምሽት 4:00 ሰዓት ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን ለአል-ዐይን አማርኛ ዜና አረጋግጠዋል፡፡
የድርጊቱን ምንነት ማወቅ የሚያስችሉ ተጨማሪ ተስፋሰጪ ሁኔታዎች መኖራቸውንና ማጣራቱም እንደሚቀጥል ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ተማሪው ትናንት ጠዋት ነበር ደሴ በሚገኘው የዩኒቨርስቲው ዋና ቅጥረ ግቢ ህንጻ ቁጥር 41 አካባቢ ተመትቶ ህይወቱ ማለፉ የተነገረው፡፡
በህንጻው አካባቢ ተፈጥሮ ነበር በተባለው ችግር የዩኒቨርስቲውን የጥበቃ ጓድ አባል ጨምሮ ሁለት ሰዎች ተጎድተው እንደነበርም ዶ/ር አባተ ተናግረዋል፡፡
“ጥቃቱ ከብሄር ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ብናስብም ይህ ነው የሚባል መንስዔን ግን በእርግጠኝነት ለማስቀመጥ አንችልም”ሲሉም ነበር ስለ ሁኔታው የገለጹት፡፡
የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተማሪውን ከመቱ በኋላ ወደ ህንጻው መግባታቸውን የግቢው የጸጥታ ኃይል ለዩኒቨርስቲው የአመራር አካላት ቢያስታውቅም የፈጻሚዎቹን ማንነት በቶሎ ለማወቅ ሆነ ጥቆማን ለማግኘት አልተቻለም ነበር፡፡
ከ90 በላይ የክልሉ የአድማ ብተና እና ከ55 በላይ የፌዴራል ፖሊስ በድምሩ ከ145 በላይ የጸጥታ አካላት በዙሪያው ባሉበት ግቢ፤ ማንም ሁኔታውን ሊመለከት በሚችልበት ሁኔታ ጠዋት ይህ መፈጠሩ አሳዛኝ ብቻም ሳይሆን ነውር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ተማሪው ተመታ በተባለበት ህንጻ ላይ ያሉ ተማሪዎች እንዲያጋልጡ ጥያቄ ስለመቅረቡም ገልጸዋል፡፡
ይህ የማይሆንና ተማሪዎቹ የድርጊቱን ፈጻሚዎች የማያጋልጡ ከሆነ ግን ሰው እየሞተ መቀጠልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ግቢ መዝጋት ስለማንችል የህንጻውን ተማሪዎች “በሙሉ እናባርራቸዋልን” ሲሉም ነበር ፕሬዝዳንቱ ያስታወቁት፡፡
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በብሔር፣ በፖለቲካና አልፎ አልፎም ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ተማሪዎችን እስከሞት ለሚያደርስ አደጋ ሲያጋልጡ፣ ሀገሪቱን ለደህንነት ስጋት መዳረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲዎችን ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ መንግስት ከመደበኛ የዩኒቨርሲቲ ጥበቃዎች በተጨማሪ በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ ወስኗል፤ የፌዴራል ፖሊሶችም የዩኒቨርሲቲ ግቢዎችን በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የደረሰው ችግር መንግስት ዩኒቨርሰቲዎች በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ ከወሰነ በኋላ ነው፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርሲቲዎች ለግጭት መከሰት አስተዋጽኦ አለዉ ያለውን የተማሪዎችን የወጭ መጋራት ክፍያ ማስቀረቱን በዛሬው እለት አስታውቋል፡፡