የሶሪያ አማጽያን ከበሽር አላሳድ መወገድ በኋላ መንግስት ለመመስረት ጥረት እያደረጉ ነው
አማጽያኑ በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ከቀድሞ ባለስልጣናት እና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር እየተወያዩ ነው ተብሏል

በዋና ከተማዋ ደማስቆ 25 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የእስራኤል ጦር በፈራረሰችው ሀገር መንግስት ምስረታ ላይ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል
ከ50 አመታት በላይ የቆየውን አላሳድን አስተዳደር የጣሉት የሶሪያ አማጽያን መንግስት ለመመስረት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ታውቋል፡፡
የአሳድ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ጃላሊ በሰሜናዊ ምዕራብ ሶሪያ በአማጺያን ቁጥጥር ስር ለሚገኘው “የድሕነት መንግስት” በአማጺያን ለሚመራው አስተዳደር ስልጣን ለመስጠት ተስማምተዋል።
አቡ መሀመድ አል ጎላኒ በመባል የሚታወቁት የዋናው አማጺ ቡድን አዛዥ አህመድ አል ሻራ ከጃላሊ እና ምክትል ፕሬዝዳንት ፋይሰል መቅዳድ ጋር በሽግግር መንግስቱ ላይ መነጋገራቸውን ሮይተርስ ስለውይይቱ የሚያውቁ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ስልጣን ለማስረከብ ፈቃደኛ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ጃላሊ ርክክብ ለመፈፀም ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል።
የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የሽግግር መንግስቱ የሚመራው “የድሕነት መንግስት” የሚባለው ስብስብ ሃላፊ መሀመድ አልበሽር ሊሆን እንደሚችል እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡
ለ13 አመታት በተደረገው ጦርነት ያልተንቀሳቀሰው መንበር ለብዙዎች ባስገረመ ሁኔታ በ12 ቀናት ውግያ መውደቁን ተከትሎ ቀጠናው እና አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ቀጣይ ምን ሊሆን እንደሚችል በስጋት እንዲጠባበቁ አድርጓል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሰኞ እለት በዝግ ባደረገው ስብሰባ አሁንም ከሁኔታዎች ፍጥነት አንጻር ዲፕሎማቶች በድንጋጤ ውስጥ እንደሚገኙ እና ቀጣይ ሀገሪቷን ወደ መረጋጋት ሊወስዱ በሚችሉ ነጥቦች ላይ ምክር ቤቱ መወያየቱ ተሰምቷል፡፡
በተመድ ምክትል የአሜሪካ አምባሳደር ሮበርት ዉድ "ይህ ለሶሪያ ህዝብ የማይታመን ጊዜ ነው ሁኔታው ወዴት እንደሚሄድ እየተከታተልን እንገኛለን፤ በሶሪያ ውስጥ የሶሪያን ህዝብ መብት እና ክብር የሚያስከብር አስተዳደር ይኖር ይሆን?" ሲሉ ጥያቄ አዘል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
"ሶሪያውያን ነጻነት፣ እኩልነት፣ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት በጉጉት እየጠበቁ ናቸው፤ ሀገራችንን እንደገና ለመገንባት እና የተሻለች ሶሪያን ለማስተዋወቅ የሚደረጉ ጥረቶችን እንቀላቅላለን" ያሉት ደግሞ በተመድ የሶሪያ አምባሳደር ኩሲ አልዳሃክ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል የሶሪያን ድንበር ጥሳ እያደረገች በምትገኘው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከደማስቆ በስተደቡብ ምዕራብ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደምትገኝ የሶሪያ የደህንነት ምንጮች በዛሬው እለት ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ግብፅ፣ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያ የቴልአቪቭን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አውግዘዋል ፤ሳዑዲ አረቢያ እርምጃው "የሶሪያን ደህንነት እና የጸጥታ ሁኔታ የማሻሻል እድል ያበላሻል" ስትል ተናግራለች።
የክልሉ የጸጥታ ምንጮች እና አሁን በወደቀው የሶሪያ ጦር ውስጥ ያሉ መኮንኖች እንዳሉት የእስራኤል ከባድ የአየር ጥቃት በሶሪያ ውስጥ ባሉ ወታደራዊ ተቋማት እና የአየር ማረፊያዎች ላይ ዛሬ ሌሊት ቀጥሏል፡፡
“በደርዘን የሚቆጠሩ ሄሊኮፕተሮች እና ጄቶች እንዲሁም በደማስቆ እና አካባቢው የሪፐብሊካን ጥበቃ ንብረቶች ወድመዋል። ከሶሪያ ጦር ንብረት ምንም አልቀረም ማለት ይቻላል” ብለዋል ።
ደህንነቷን ለማስጠበቅ የተወሰኑ እና ጊዜያዊ እምርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ የገለጸችው እስራኤል የአየር ጥቃቷን ለቀናት እንደምትቀጥ፣ ነገር ግን በሶሪያ ግጭት ውስጥ ጣልቃ እንደማትገባ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተናግራለች።