እስራኤል የአሳድ አገዛዝ ማብቃቱን ተከትሎ ወደ ሶሪያ ዘልቃ ገባች
የእስራኤል ጦር ከጦርነት ነጻ በሆነው የጎላን "በፈር ዞን" ውስጥ የሚገኙ አምስት መንደሮች ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ አሳስቧል

ኔታንያሁ አማጺያን ሶሪያን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ከደማስቆ ጋር በ1974 የተደረሰው ስምምነት "አብቅቶለታል" ብለዋል
የሶሪያ አማጽያን ደማስቆን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ እስራኤል የሶሪያን ድንበር ጥሳ ገብታለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሀገራቸው ጦር ከጦርነት ነጻ የሆነውን የጎላን ኮረብታ (የሶሪያ ክፍል) በጊዜያዊነት መቆጣጠሩን ተናግረዋል።
ኔታንያሁ የእስራኤል ጦር የጎላን ኮረብታዎች "በፈር ዞን"ን እንዲቆጣጠር ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውንና እስራኤል በሀይል በተቆጣጠረችው የጎላን ክፍል የማዘዣ ጣቢያ መቋቋሙንም ነው የገለጹት።
"ማንኛውም አፍራሽ ሃይል በድንበራችን አካባቢ እንዲደራጅ አንፈቅድም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እስራኤልና ሶሪያ ግጭት ውስጥ ላለመግባት በ1974 የደረሱት ስምምነት አማጺያን ሀገሪቱን በመቆጣጠራቸው እንደፈረሰም አብራርተዋል።
ተቀማጭነቱን ብሪታንያ ያደረገው የሶሪያ ጦርነትን የሚከታተል ቡድን የሶሪያ ጦር ከጦርነት ነጻ በሆነው ክልል ውስጥ ከምትገኘው ኩኔትራ ግዛት መውጣቱን ጠቁሟል።
ኒውዮርክ ታይምስም የእስራኤል ባለስልጣናት ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው እስራኤል ከጦርነት ነጻ ከሆነው ክልል ተሻግራ ወደ ሶሪያ ለመግባት ባለፉት ሁለት ቀናት ጥረት እያደረገች መሆኑን ዘግቧል።
ከደማስቆ በ60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የጎላን ኮረብታ እስራኤልና ሶሪያን ለአመታት ያወዛግባል።
እስራኤል ጎላንን በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት ማገባደጃ ላይ መያዟና በ1981 የግዛቷ አካል አድርጋ ማወጇ ይታወሳል። ይሁን እንጂ አለማቀፉ ማህበረሰብ የጎላን ኮረብታዎች የእስራኤል ሉአላዊ ግዛት አካል መሆኑን እውቅና አይሰጠውም። አሜሪካ በ2019 በወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለእስራኤል እውቅና መስጠታቸው የሚታወስ ነው።
የሶሪያ ሃይሎች በ"ሃያት ታህሪር አል ሻም" (ኤችቲኤስ) መሪነት ትናንት ጠዋት ደማስቆን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የበሽር አል አሳድ እና የአባታቸው የ53 አመታት የስልጣን ዘመን ማብቃቱ ተገልጿል።
የአሳድ አገዛዝ የወደቀበት እለት "በመካከለኛው ምስራቅ ታሪካዊ ቀን" ያሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፥ የአገዛዙ መውደቅ ትልቅ እድል እንዳለው ሁሉ አደጋ መደቀኑን መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
እስራኤል የአሳድ ደጋፊዎች በነበሩት ኢራን እና እንደ ሄዝቦላህ ያሉ ቴህራን የምታስታጥቃቸው ቡድኖች ላይ የፈጸመችው የአየር ጥቃት አሁን በሶሪያ ለታየው ለውጥ ድርሻ እንዳለው በመጥቀስም፥ ከእስራኤል ጋር በሰላም ለመኖር ለሚፈልጉ ሶሪያውያን "የሰላም እጃችን እንዘረጋለን" ብለዋል።
የእስራኤል ጦር ከጦርነት ነጻ በሆነው የሶሪያ ጎላን ክፍል የገባው በጊዜያዊነት ቢሆንም ደማስቆን የተቆጣጠረው ሃይል የሚሰጠው ምላሽ ቀጣይ እርምጃችን ይወስናልም ነው ያሉት።
"ሶሪያን ከተቆጣጠረው አዲስ ሃይል ጋር የጎረቤትና ሰላማዊ ግንኙነት መመስረት እንፈልጋለን፤ ይህ ካልሆነ ግን እስራኤል እና ድንበሯን ለማስጠበቅ የትኛውንም እርምጃ እንወስዳለን" በማለትም ዝተዋል።
የበሽር አል አሳድ የ53 አመታት አገዛዝ የጣለውን የአንድ ሳምንት ፈጣን እንቅስቃሴ የመራው አቡ ሞሀመድ አል ጃውላኒ ቤተሰቦች የትውልድ መንደር የጎላን ኮረብታዎች ነው።
ጃውላኒ የወላጆቹን የትውልድ ቀዬ የግዛቷ አካል ላደረገችው እስራኤል የሚሰጠው ምላሽ ይጠበቃል።