እስራኤል በደማስቆና ሌሎች የሶሪያ ከተሞች የአየር ጥቃት ፈጸመች
በብሪታንያ የሚገኘው የሶሪያ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋም እስራኤል ከ100 በላይ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጿል

ቴል አቪቭ የሶሪያ ስትራቴጂካዊ የጦር መሳሪያዎች "በአክራሪዎች እጅ እንዳይገባ አወድማለሁ" ስትል መዛቷ ይታወሳል
እስራኤል በሶሪያ የምትፈጽመውን የአየር ጥቃት ቀጥላለች።
የሶሪያ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ደማስቆን ጨምሮ በተለያዩ የሶሪያ ከተሞች በደርዘን የሚቆጠሩ የአየር ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
ተቀማጭነቱን ብሪታንያ ያደረገው የሶሪያ የሰብአዎ መብቶች ተቆርቋሪ ተቋም (ኤስኦኤችአር) እስራኤል ባለፉት ሁለት ቀናት በሶሪያ ከ100 በላይ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች ብሏል።
ከሶሪያ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ ምርምር የሚደረግበት ተቋምም የጥቃቱ ኢላማ መሆኑ ነው የተዘገበው።
እስራኤል የበሽር አል አሳድ አገዛዝ መውደቅን ተከትሎ የሀገሪቱ ጦር መሳሪያዎች "በአክራሪዎች እጅ እንዳይገባ" ጥቃት እንደምትፈጽም ዝታለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የአየር መቃወሚያ ስርአቶች፣ ሮኬቶችና ሚሳኤሎችን ጨምሮ የሶሪያን ስትራቴጂካዊ የጦር መሳሪያዎች እናወድማለን ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ትናንት በሶሪያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የመከረ ሲሆን በቀጣይ ቀናት የአቋም መግለጫውን እንደሚያወጣ አስታውቋል።
በተመድ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች ቁጥጥር ድርጅትም የሶሪያ ባለስልጣናት የበሽር አል አሳድ አስተዳደር አከማችቶታል የሚባለው የኬሚካል ጦር መሳሪያ ደህንነት እንዲጠበቅ አሳስቧል።
ሶሪያ ምን ያህል መጠን ያለው የኬሚካል ጦር መሳሪያ እንዳላት በግልጽ ባይታወቅም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ገዳዮቹን ኬሚካሎች በብዛት እንዳከማቸ ይታመናል።
ደማስቆ ሳሪን በተሰኘው ኬሚካል ከ1 ሺህ 400 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ በፈረንጆቹ 2013 የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን ከሚቆጣጠረው አለማቀፍ ድርጅት ጋር ስምምነት መፈጸሟ ይታወሳል።
ሀገሪቱ ከ1 ሺህ 300 ቶን በላይ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን ማውደሟን ብትገልጽም በተለያየ ጊዜ እንደተጠቀመችባቸው ይነገራል።
ቢቢሲ በ2018 ያደረገው ምርመራ እንደሚያሳየው ሶሪያ ከ2014 እስከ 2018 ድረስ በጥቂቱ 106 ጊዜ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን ተጠቅማለች።
የመንግስታቱ ድርጅት የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ቁጥጥር ተቋምም ደማስቆን የተቆጣጠሩት ሀይሎች በሽር አል አሳድ ያከማቹትን የኬሚካል ጦር መሳሪያ ደህንነት ካላስጠበቁ አደጋው የከፋ ነው ብሏል።