ታሊባን በሴቶች መብት ስም የሚጣለው ማዕቀብ አፍጋኒስታናውያንን እየቀጣ ነው አለ
በታሊባን በሴቶች ላይ ያለው አያያዝ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ይገለጻል
የካቡል ቃል አቀባይ በእስልምና ህግ አተረጓጎም መሰረት ታሊባን የሴቶችን መብት እያከበረ ነው ብለዋል
እንደፈረንጆቹ ነሃሴ 2021 ምዕራባውያን አፍጋኒስታንን ለቀው መውጣታቸው ተከትሎ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ በትረ ስልጣን የጨበጠው ታሊባን፤ አፍጋኒስታናውያን ሴቶች ከፓርኮች ፣ ጂሞች እንዲሁም ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች የተገለሉ እንዲሆኑ የሚያስችል ደምብና አሰራር ዘርግቶ ሀገሩቱን በማስተዳደር ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህም ታሊባን በአፍጋኒስታን ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ያለው አያያዝ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሊሆን እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ባለሙያዎች ቡድን ገልጿል፡፡
የተመድ የአፍጋኒስታን ልዩ ራፖርተር ሪቻርድ ቤኔት እና ሌሎች የተመድ ዘጠኝ ኤክስፐርቶች ባደረጉት ግምገማ በሀገረቱ እየተስተዋለ ያለው የሴቶች አያያዝ አፍጋኒስታን በተካፈለችበት የሮም ስምምነት መሰረት "የጸታ ስደት" ሊሆን ይችላል ማለታቸው ሮይተረስ ዘግቧል።
ባለሙያዎቹ ሴቶች በቤታቸው ውስጥ መቆየታቸው "ከእስር ቤት ጋር እኩል ነው" በማለት የቤት ውስጥ ችግር እና የአእምሮ ጤና ችግሮች መጨመር እንደሚያስከትል ተናግረዋል፡፡
የተመድ ባለሙያዎች ቡድን ግምገማ ይህን ያመላክት እንጅ የካቡል ባለስልጣናት ግን ክሱን እንደማይቀበሉት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
በተመድ መድረክ ለቀረበው ሪፖርት ምላሽ የሰጡት የታሊባን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አብዱል ቃሃር ባልኪ “የባበሩት መንግስታት ድርጅት በሴቶች መብት እና እኩልነት ስም በሚጥለው ማዕቀብ ንጹሃን አፍጋኒስታናውያንን እየቀጣ ነው” ብተለዋል፡፡
ምዕራባውያን እንደሚሉት ሳይሆን በእስልምና ህግ አተረጓጎም መሰረት ታሊባን የሴቶችን መብት እንደሚያከብርም ተናግረዋል፡፡