በወቅቱ ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ ካቡልን ለቀው መሰደዳቸው አይዘነጋም
ታሊባን አፍጋኒስታንን መልሶ የተቆጣጠረበትን አንደኛ ዓመት እያከበረ ነው።
ከስልጣን ከተወገደበት ከ20 ዓመታት በፊት ጀምሮ በትጥቅ ትግል ላይ የነበረው ታጣቂው ቡድን መልሶ ስልጣን ለመቆጣጠር የቻለበትን ወታደራዊ ድል ነው እያከበረ ያለው።
አሜሪካ ለቃ መውጣቷን ተከትሎ ልክ የዛሬ ዓመት የሃገሪቱን ዋና ከተማ ካቡልን መልሶ መቆጣጠሩና የራሱን መንግስት መመስረቱ ይታወሳል።
በወቅቱ ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ ካቡልን ለቀው ወደ አረብ ኤሚሬት ሸሽተው እንደነበርም የሚታወስ ነው።
የታሊባንን አገዛዝ በመሸሽ ከሃገራቸው ለመውጣት ትንቅንቅ ላይ የነበሩ በርካታ አፍጋናውያን ህይወት መቀጠፉም አይዘነጋም።
አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያንን ኃይሎችም ጦራቸውንና ዜጎቻቸውን ለማስወጣት እስከ ወርሃ ነሐሴ መጨረሻ ጥድፊያ ላይ ነበሩ።
ታሊባን ስልጣን ከያዘ በኋላ መጠነኛ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም በተለይም በሴቶችና በትምህርት ጉዳይ ላይ ጥብቅ ቁጥጥርን ማድረግ መቀጠሉ ይነገራል።
ሃገሪቱን ያደቀቀው ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ከ30 ሚሊዮን በላይ አፍጋናውያን ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር መዳረጋቸውንም ነው ኤ.ኤፍ.ፒ የዘገበው።
ቡድኑ ወደ ስልጣን ሲመጣ በምዕራባውያን እገዳ ስር ያለውና በውጭ የተከማቸው የሃገሪቱ ሐብት እንዲለቀቅለትና ዓለም አቀፍ ድጋፎች እንዲደረጉለት መጠየቁ ይታወሳል።