ለጋሾች ተከማችቶ የነበረውን 280 ሚሊየን ዶላር ለአፍጋኒስታን እንዲለቀቅ ከስምምነት ደረሱ
በአፍጋኒስታን ያለው ችግር “በምድር ላይ የተከሰተ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ነው” ተብሎለታል
የዓለም የምግብ ፕሮግራም “23 ሚልየን የአፍጋኒስታን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል ብሏል
ዓለም አቀፍ ለጋሾች ተከማችቶ ነበረው የ280 ሚልየን ዶላር ገንዘብ ለአፍጋኒስታን የምግብ እና ጤና እርዳታ ድጋፍ እንዲውል ከስምምነት መድረሳቸውን የዓለም ባንክ አስታወቀ።
አፍጋኒስታን በታሊባን ስር ከወደቀችበት ካለፈው ወር ወዲህ፤ ከምዕራባውያን ታገኝ የነበረውን ድጋፍ ስለተቋረጠ በከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ተዘፍቃ የምትገኝ ሀገር ናት።
50 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ ለከባድ የረሃብ አደጋ እንደተጋለጠ እንደሁም 3 ሚልየን ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት እየተሰቃዩ እንደሚገኙም የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሪፖርት ያመለክታል።
የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ታሊባንን እንደመንግስት መቀበላቸውን ይፋ ባያደረጉም፤ አሜሪካና አጋሮቿ ለሀገሪቱ ያደርጉ የነበረውን የ10 ቢልየን ዶላርን እንዲሁም አይ.ኤም.ኤፍ ሲያመቻቸው የነበረ የብድር እድል ለጊዜው እንዳቆሙት ይጠበቃል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም 23 ሚልየን የሚሆኑ የአፍጋናውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል።
በአፍጋኒስታን ያለው ችግር “በምድር ላይ የከፋው ሰብዓዊ ቀውስ ነው” ሲል ገልጾታል።
አሁን ለጋሾች የተስማሙበትና ከዓለም ባንክ ይለቀቃል የተባለው ገንዘብ፤ ተመድ ድርጅቶች ወደ ሆኑት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ዩኒሴፍ ይዛወራልም ነው የተባለው።
የዓለም የምግብ ፕሮግራምና ዩኒሴፍ በአፍጋኒስታን ያለቸውን የሎጂስቲክስ እና የሰራተኛ አቅም በመጠቀም በቀጥታ ለአፍጋኒስታን ህዝብ እንደሚያደርሱትም የዓለም ባንክ ገልጿል።
ከሚዘዋወረው ገንዘብ 100 ሚልየን ዶላሩን ዩኒሴፍ ወስዶ ለጤና አገልግሎት የሚውል ሲሆን፤ 180 ሚልየን ዶላሩ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚሰጥ መሆኑን ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።