ቴስላ በሚቀጥለው አመት የሰው መሰል ሮቦቶች ምርት እንደሚጀምር አስታወቀ
ሮቦቶቹ ያለምንም ድጋፍ በራሳቸው መንቀሳቀስ የሚችሉ ሲሆኑ በፋብሪካዎች ላይ ሰዎች የሚያከናውኗቸውን ስራዎች እንደሚሰሩ ይጠበቃል
አንድ ሮቦት ከቴስላ መኪና ባነሰ ዋጋ ለገበያ እንደሚቀርብ ኩባንያዎ አስታውቋል
ቴስላ በሚቀጥለው አመት የሰው መሰል ሮቦቶች ምርት እንደሚጀምር አስታወቀ።
ቴስላ በሚቀጥለው አመት የሰው መሰል ሮቦቶችን ምርት እንደሚጀምር የድርጅቱ ባለቤት እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤለን መስክ አስታውቋል፡፡
ከ2021 ጀምሮ ቴስላ ጥናት እና ምርምር ሲያደረግባቸው የነበሩት “ሂዩማኖይድ” የተሰኙት ሰው መሰል ሮቦቶች በራሳቸው መንቀሳቀስ የሚችሉበት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ደረጃ እና ትእዛዛትን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት አሰራር ጥናት መጠናቀቁን ገልጿል፡፡
ከመጪው አመት ጀምሮ ወደ ምርት ሂደት እንደሚገቡ የተነገረላቸው ሮቦቶች በቅድሚያ በኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ኩባንያ ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የገለጸ ሲሆን ከ2025 አመት መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ ወደ አለም አቀፍ ገበያ እንደሚወጡ ነው ይፋ ያደረገው፡፡
“ኦፕቲመስ” እና “ባምብልቢ” የተሰኙት እነኚህ ሰው መሰል ሮቦቶች ከዚህ ቀደም አገልግሎት ላይ ከዋሉት ሮቦቶች የሚለያቸው በራሳቸው አቅም የሚያሰላስሉበት እና ትእዛዛትን በቃል እና በኮምፒውተር ተቀብለው የሚተገብሩበት አዕምሮ እንደተገጠመላቸው ተሰምቷል፡፡
በ2025 መጨረሻ ለገበያ ሲቀርቡ የአንድ ሮቦት ዋጋ ከ20ሺ ዶላር ያነሰ ዋጋ ተቆርጦላቸዋል፡፡
ከደህንነት ጋር በተገናኘ ሮቦቶቹ ወደ ሰዎች ህይወት መቀላቀላቸው ስጋትን እንደሚፈጥር የሚያነሱ የሮቦቶችን ምርት ሲቃወሙ፣ ሌሎች ደግሞ የሰዎችን ስራ የመንጠቃቸው እድል ከፍተኛ በመሆኑ በርካቶች ከስራ ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከፍተኛ ስጋት አድሮባቸዋል፡፡
ሮቦቶቹ የሰዎችን እንቅስቃሴ ፣ አካሄድ ፣ የፊት ስሜት አገላለጽ እና በፋብሪካ ምርት ስራዎች ላይ ሰዎች የሚሰሯቸውን ስራዎች በሙሉ በተሻለ ቅልጥፍና እና ጥራት ማከናወን የሚችሉ ናቸው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ሮቦቶቹ በባር አስተናጋጅነት ፣ በእርጅና እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ለማገልገል ፣ በጠላቂ ዋናተኝነት ፣ በስብሰባ መድረክ መሪነት እንዲሁም በአጠቃላይ በትምህርት ፣ በጤና ፣ በኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፍ ላይ መሰማራት የሚችሉ ናቸው ተብሎላቸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የሰራተኛ ሀይል እጥረት ባለባቸው ጃፓንን በመሳሰሉ ሀገራት በሆንዳ እና ሃይዮንዳይ ኩባንያዎች አሰልቺ እንዲሁም ተደጋጋሚ በሚባሉ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን የቻሉት ሮቦቶች ቴስላ አመርትባቸዋለሁ ባለው የቴክኖሎጂ ደረጃ ወደ ገበያ የሚወጡ ከሆነ ከፍተኛ ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ቴስላ እንዳስታወቀውም የሮቦቶቹ ሽያጭ ድርጅቱ እስከዛሬ ካመረታቸው ምርቶች የበለጠ ሽያጭ ሊኖራቸው እንደሚችል ገምቷል፡፡
በ2023 የሰው መሰል ሮቦቶች አለም አቀፍ የገበያ ድርሻ 1.8 ቢሊየን ሲሆን በመጪዎቹ አምስት አመታት ይህ ቁጥር ወደ 13 ቢሊየን ዶላር እንደሚያድግ የገበያ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡