ባለ 6 እግሩ ሮቦት ከሰዎች በሚሰጠው የድምጽ ትእዛዝ ያለምንም ችግር መጓዝ ይችላል
የቻይናው ሻንጋይ ጂአዎ ቶንግ ዩኒቨርስቲ አይነ ስውራንን መንገድ የሚመራ አዲስ የሮቦት ቴክኖሎጂ አስተዋውቋል።
ባለ 6 እግሩ ሮቦት መንገድ ጠቋሚ ሴንሰር፣ የሌዘር ራዳር ቴክኖሎጂ እና የናቭጌሽን ሲስተም የተገጠመለት ሲሆን ከሰው በሚሰጠው የድምጽ ትዕዛዝ ካሰቡት ቦታ ያለምንም ችግር ማድረስ የሚችል ነው ተብሏል።
ከቴክኖሎጂው ፈጣሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ጃው ፌንግ ሮቦቱ በተለይ ለጉዞ አይንን ተክቶ ማገልገል የሚችል ነው ብለውታል።
የትራፊክ መብራቶችን እና ሌሎች የደህንነት ማስጠንቀቂያዎችን ጠንቅቆ የሚያውቀው ሮቦት በተጨማሪም አስቸጋሪ የመንገድ ላይ ሁኔታዎችን በመለየት አይነስውራን በመንገድ ላይ ከሚያጋጥማቸው አደጋ ይከላከላል ተብሎለታል።
ሮቦቱ በሚኖርበት ከተማ ላይ ያሉ ቤተመጽሀፍቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ ቤተእምነቶችን እና ሌሎችንም በኢንተርኔት አማካኝነት መዝግቦ የሚያስቀምጥ ሲሆን ከሰዎች በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት መጓዝ የሚችል ነው።
የቴክኖሎጂው ባለቤቶች ሮቦቱ የተገጠሙለት 6 እግሮች መሰናክሎችን እና የማይመቹ መንገዶችን እና ደረጃዎችን ያለ ችግር እንዲጓዝ የሚያደርጉት ነው።
ከዚህ ባለፈም በተመጠነ የጉዞ ፍጥነት በሰከንድ 3 ሜትሮችን መጓዝ የሚችል ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ባለቤቱ በሚፈልገው የጉዞ መጠን እንዲፈጥን አልያም እንዲዘገይ የሚነገረውን ትዕዛዝ ይቀበላል።
በተጨማሪም አይነ ሰውራን የጤና ችግር እና ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥማቸው በተገጠመለት አላርም የእርዳታ ጥሪን ማድረግ ይችላል።
እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ ከሆነ በቻይና 17.31 ሚሊየን አይነ ስውራን የሚገኙ ሲሆን በተለምዶ አይነ ስውራን ከሚጠቀሙት መንገድ ጠቋሚ በትር (ኬን) ባለፈ የሰለጠኑ ውሾችን ለመንገድ መሪነት ይጠቀማሉ፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በቻይና የሚገኙት የሰለጠኑ ውሾች ቁጥር 40 ሺ ብቻ ነው።
እነዚህ ውሾች ለስልጠና እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሚጠይቁት ወጭ አንጻር አዲሱ የሮቦት ቴክኖሎጂ ወደ ገበያ ሲገባ ተመራጭ እንደሚሆን ተነግሯል።
ሮቦቱ በአሁኑ ወቅት የመስክ ሙከራ ላይ ሲሆን ዩኒቨርስቲው ለገበያ ገና ባያቀርበውም 20 ትእዛዞችን መቀበሉን ገልጿል።
በአለም አቀፍ ደረጃ 50 ሚሊየን አይነ ስውራን እንዳሉ ይነገራል ከዚህ ውስጥ 85 በመቶዎች ቢያንስ በወር አንድ ግዜ የተለያዩ አደጋዎች ያጋጥሟቸዋል።