የደራሼ ባህላዊ የ ‘ፊላ’ ፌስቲቫል በጊዶሌ እየተካሔደ ነው
‘ፊላ’ ከሙዚቃ መሳሪያነቱ ባለፈ ፣ በደራሼዎች ዘንድ ልዩነቶች የሚወገዱበት ባህላዊ ክዋኔ ነው
የ ፊላ ፌስቲቫል ስያሜውን ያገኘው ከደራሼዎች ተወዳጅ የትንፋሽ መሳሪያ ነው
‘ፊላ’ ባለ ሰባት ኖታ የደራሼዎች ባህላዊ የትንፋሽ መሳሪያ ነው፡፡ ይህ ተወዳጅ የሙዚቃ መሳሪያ የጥጋብ ፣ የሰላም ፣ የደስታ ፣ የአንድነት ፣ የፍቅር እና የይቅርታ መገለጫ እንደሆነ ይገለጻል፡፡ በደራሼ በሃይማኖት እና በብሔር ልዩነት ሳይፈጠር ቅራኔዎች ተወግደው የፊላን በዓል በአንድነት ያከብራሉ፡፡
ይህ ባህላዊ ጨዋታ በሚካሔድበት ወቅት አለመግባባት እና ቅራኔ ያላቸው ሰዎች ልዩነታቸውን ትተው ፣ እርቅ በመፈጸም በአንድነት ይጨፍራሉ፡፡ ፊላ ከሙዚቃ መሳሪያነቱ ባለፈ ፣ በደራሼዎች ዘንድ ልዩነቶች የሚወገዱበት ባህላዊ ክዋኔ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡
በባህላዊው መሳሪያ-ፊላ ስም የተሰየመውና የደራሼ ህዝብ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ያግዛል የተባለ የፊላ ፌስቲቫል በጊዶሌ ከተማ መካሄድ ከጀመረ 3ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ይህ ባህላዊ ፌስቲቫል ከጥምቀት በዓል ማግስት የሚካሔድ ሲሆን በዛሬው ዕለት ሦስተኛው የፊላ ፌስቲቫል መካሔድ ጀምሯል፡፡
የደራሼ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አመኑ ቦጋለ፣ የደራሼ ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ የማድረጉ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አብሮነት፣ አንድነትና ትብብር የደራሼ መገለጫዎች እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ አመኑ ፣ ፌስቲቫሉ የተዘጋጀው ወጣቱ እሴቶቹን አውቆ እንዲጠብቅ ለማገዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለሶስት ቀናት በሚቆየው ፌስቲቫል በልዩ ወረዳው የሚገኙ የደራሼ፣ ኩስሜ፣ ሞስዬና ማሾሌ ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች እተዋወቁ ነው፡፡