“የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ለብሄራዊ ጉዳዮች የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ነው፡፡”
“የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ለብሄራዊ ጉዳዮች የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ነው፡፡”
በመጋቢት 2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለትና በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የህዳሴ ግድብ በ5 ዓመታት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ዕቅድ ቢያዝለትም ግንባታው ግን ከመጠን በላይ በመዘግየቱ መንግስት አዲስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የቀድሞው የኢህአዴግ ሹመኞች የኤሌክትሮሜካኒካል ስራውን ለብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን የግንባታው መዘግየት ችግር ልየታ ተከናውኖ ነበር፡፡
የመዘግየቱ ምክንያት ሜቴክ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በእርሱ ስር ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ንዑስ የግንባታ ተቋራጮች ዋና ተቋራጭ እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ መተላለፉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
በረጅሙ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ ታዲያ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ከመሆን አልዳነም፡፡ ድንበር ተሸጋሪ ወንዞች እንደሚያወዛግቡት ሁሉ ዓባይም ውዝግብ አስነስቷል፡፡
በአፍሪካም በገንቢዋ ኢትዮጵያና ታሪኬም ህይወቴም ዓባይ ነው በምትለው ግብጽ መካከል ውዝግብና ክርክር ከተነሳ ቆይቷል፡፡ ግብጾች የአስዋንን ያህል ታላቁ የህዳሴ ግድብን በቅርብ ይከታተሉታል፡፡ በቅርቡ ደግሞ አዲስ አበባ፣ካይሮና ካርቱም ሲደራደሩ የዓለም ባንክና አሜሪካ እንዲገኙ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
አሁንም የአሜሪካው ድርድር አላለቀም፡፡ የሦስቱም ሃገራት የውሃ ሚኒስትሮች ዋሸንግተን ናቸው፡፡
ግብጻውያን ምሁራን ፣ፖለቲከኞች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ግብጽን በተለያዩ ሃገራት የሚወክሉ ዲፕሎማቶች፣ ዲያስፖራዎችና ሌሎችም ግብጻውያን በግድቡ ዙሪያ በየደቂቃው አስተያየት ይሰጣሉ፤ከሃገራቸውም ጎን ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያንስ?
ኢትዮጵያ ግድቡን በጀመረችበት ዕለት በ7ኛው ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2010 ላይ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰይማለች፡፡ በሃገሪቱ ያሉት አመጾች አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር፣አዲስ አፈጉባዔ፣አዲስ ፕሬዚዳንትና አዳዲስ የካቢኔ አባላትን ወደ መንበር አምጥተው ብቻ ዝም አላሉም፡፡
ይልቁንም አዳዲስ ግጭቶችን፣አዳዲስ የህዝብ ጥያቄዎችን እና አለመረጋጋቶችን ፈጥረዋል፡፡
በእርግጥ በምሁራን እይታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋማት እንዲሻሻሉ፣በሃገሪቱ ያሉ የህሊና እስረኞች እኒዲፈቱና ከሃገራት ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል ማድረጋቸው ይነሳል፡፡
ይሁን እንጂ፣ በምሁራኑ አስተያየት፣ የተደረጉት ማሻሻያዎችና የለውጥ እርምጃዎች ኢትዮጵያን ማረጋጋት አልቻሉም፡፡ ይልቁንም ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ከማተኮር ይልቅ በብሔርና በማንነት ላይ ትኩረት ተደረገ፡፡በዚህ መሃል ታዲያ እንደ ዓባይ ያሉ ግዙፍ ፕሮጄክቶች በብዙዎች ትኩረት ሳያገኙ ቀሩ የሚሉም አሉ፡፡
በሃገሪቱ በተደረገው ማሻሻያ በውጭ ሃገራት የነበሩና በመሳሪያ ጭምር መንግስትን ለመውጋት አስበው የነበሩ ሁሉ ወደ ሃገር ቤት ገብተው አሁን ቁጥራቸው ከ100 በላይ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ፓርቲዎቹ የመብዛታቸውን ያህል ታዲያ ለሃገራዊ ጥያቄዎች ትኩረት አለመስጠታቸው ያስወቅሳቸዋል፡፡ የህዳሴው ግድብ፣ብሔራዊ መግባባት፣የዜጎች መፈናቀል፣የዋጋ ግሽበት፣ዲፕሎማሲና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፏቸው አናሳ ነው በሚልም ይተቻሉ፡፡
ግብጻውያን ለናይል የሚሰጡትን ትኩረት ያህል ኢትዮጵያውያን ይነጋገሩበታል ወይ የሚለው ጥያቄ በብዙዎች የሚነሳ ጉዳይ እደሆነም ይገለጻል፡፡ አሁን ላይ ብዙ የፖለቲካ ሃይሎች የሚያስጨንቃቸው እንዴት ምርጫ እናሸንፍ እንጂ እንዴት በህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ አስተዋጽኦ እናበርክት እይደለም የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች አሉ፡፡
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የዓባይን ጉዳይ በመዘገብ የሚታወቀው ስላባት ማናዬ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች በዚህ ትልቅ የቤት ስራ ላይ ዕይታቸው ችግር እንዳለበት እንደሚሰማው ያነሳል፡፡
ፓርቲዎች መንግስት ስለመሆን ከማሰብ አስቀድሞ በሃገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ ማሰብን ማስቀደም አለባቸው ይላል፡፡
ከሰሞኑ በአሜሪካ ሲደረግ ስለነበረው ድርድር ከ100 በላይ ከሚሆኑ ፓርቲዎች መካከል ስለ ድርድሩ አስተያየቱንና ስጋቱን የገለጸው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) መሆኑን መታዘብ ችለናል፡፡
አብሮነት የሕዳሴውን ድርድር አስመልክቶ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም ‹‹የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ያለው በዋጋ ሊተመን የማይችል የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ጠቃሚ ፕሮጀክት ስለመሆኑ ይገነዘባል፤ በዚህ ግድብ ላይ የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድርም የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን ትውልድ ጥቅም የሚወስን፣ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ከአስር የማያንሱ የአፍሪካ አገሮችን ጥቅም የሚመለከት ድርድር እንደሆነ አብሮነት ይገነዘባል›› ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
‹‹በህዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄድ ድርድር ይህንን ያህል ከፍተኛ የሆነ ሃገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ ያለው ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ፣ የግብፅ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አሜሪካ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አሸማጋይ ለመሆን የፈለጉበትን የድርድር ጥያቄ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያውም መቀበል አልነበረባትም፡፡ ከዚህ ድርድር ጀርባ ያሉ አገራት እና ተቋማት በሙሉ ከኢትዮጵያ ይልቅ የግብፅ ወዳጅ ናቸው›› ሲልም አብሮነት ስጋቱን መግለጹን ይፋ አድርጓል፡፡
አብሮነት ድርድሩ መጀመሪያውኑ ከአፍሪካ ማዕቀፍ ወጥቶ በእነዚህ የሩቅ እና ገለልተኛ ያልሆኑ ሃይሎች አደራዳሪነት እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነም ገልጾ፣ ከአገር ብሔራዊ ደህንነት ጋር የተያያዘ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ በጥድፊያ እና ግልፅነት በጎደለው ሁኔታ መወሰን ስለሌለበት የድርድሩን ሰነድ በስምምነት ለመቋጨት የተያዘው ጊዜ ላልተወሰነ ግዜ እንዲራዘም ጠይቋል፡፡
በዚህ በሚራዘመው ጊዜም በቂ መድረክ ተፈጥሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ከህዝብ እና ከአፍሪካ ወዳጅ አገሮች ጋር ጭምር ግልፅ ውይይትና ምክክር እንዲካሄድ፣ የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን ጉዳይ በትኩረት እንዲከታተልና ይህ ስምምነት ከእሱ ዕውቅና ውጭ በጥድፊያ እንዳይፈረም ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
ሌሎች በግድቡ ላይ ምን አሉ?
አሁንና ከአሁን ቀደም በነበረው ድርድር በግልጽ አቋሙን የገለጸው አብሮነት ሲሆን ከፓርቲው ውጭ ሌሎች አካላት በግልም ይሁን በተናጠል ማብራያ የጠየቁ፣ማሳሰቢያ የላኩም ሆነ ስጋታቸውን የገለጹ እስካሁን አልታዩም፡፡
ይህም ብዙ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ ጥቅም ላይ ያሳዩት ቸልተኝነት እንደሆን የሚቆጥሩት በርካቶች ናቸው፡፡ በእርግጥ ጥቂትም ቢሆን ጋዜጠኞች፣አክቲቪስቶች፣በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ኢትጵያውያን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡
ይህ ግን ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ላላት ሃገር እጅግ ጥቂት መሆኑን መገንዘብ እንደሚቻልም ይጠቀሳል፡፡
ግብጻውያን በሁሉም የዓለም አካባቢዎች ቢኖሩ፣ በየትኛውም ጎራ ቢሰለፉ፣ የቀድሞም ሆነ የአሁን ባለስልጣናት፣ተቃዋሚዎችም ሆኑ ደጋፊዎች የናይል ጉዳይ ጉዳያቸው ነው፡፡ በግብጽ ብዙ ፍላጎቶች አሉ፡፡ሽብረተኝነት፣የሃይማኖት አክራሪነት፣የሙስሊም ወንድማማችነት ፓርቲ ውዝግብ፣የስዊዝ ቦይን የተመለከቱ ፖለቲካዎችና ሌሎችም ልዩኘቶች አሉ፡፡
ግን ልዩነቱ ወደ ናይል አይዞርም፡፡ በናይል ጉዳይ ቀልድ የለም፡፡ ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው የውሃ ምህንድስናን በብዛት ነው የሚያስተምሩት፡፡ በግብጽ ከ4ሺ በላይ ሙዚቃዎች ናይል ናይል ይላሉ፡፡ ውሃው የሚነሳባት ኢትዮጵያ በልዩነት ውስጥም ቢሆን ከውስጧ ስለሚያልፈው ወንዝ ስለምን ዝምታን መረጠች የሚለው ትልቁ ጥያቅ ነው፡፡
መንግስትስ?
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሊ የሚመራው መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውንና የውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትሩን ስለሺ በቀለን ለድርድሩ መድቧል፡፡በጥቅሉ 11 የሃገር ልጆች ለድርድር አሜሪካ ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር የህግና የውሃ ባለሙያዎችን ይጨምራል፡፡
የሶስቱ ሀገራት ተደራዳሪዎች ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ሲወያዩ
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በጉዳዩ ዙሪ ዘገባዎችን የሚሰራው ዋለልኝ አየለ ‹‹ስለህዳሴው ብዙ ነገር ለማለት ነገሩ ሁሉ ድፍንፍን ያለ ነው፤ ግልጽ የሆነ ነገር የለም›› ይላል፡፡ መንግስት ኢትዮጵያ ጥቅሟን አስጠብቃለች እያለ በመሆኑ፣ ጥቅሟን አላስጠበቀችም ብሎ ለመናገር እንዳያመች መረጃዎችን ምሥጢራዊ አድርጓልም ይላል ጋዜጠኛው፡፡
አቶ ዋለልኝ እንደሚለው ኢትዮጵያ ጥቅሟን አስጠብቃለች እንዳይባል አደራዳሪዎቹ የግብጽ አለኝታዎች ናቸው፤ ግብጽ በምትፈልገው መንገድ ነው ነገሮች እየሄዱ ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት ላይ ነው እየተደራደረች ያለችው፤ መደራደሯ በራሱ እኮ በራስ ሀብት አለማዘዝ ነው ሲል ጉዳዩን ያብራራል፡፡
በአሜሪካ ዋሸንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፊጹም አረጋ በትዊተር አድራሻቸው እንደገለጹት፣ ቡድኑ በብዙ ጉዳዮች ላይ የመከረ ቢሆንም ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ ማዘጋጀት አለመቻሉ ታይቷል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት የምታምን ሲሆን፣ በአባይ የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሰጥ ምንም ዓይነት ስምምነት አትፈጽምም›› ሲሉ መጻፋቸው ይታወሳል፡፡
ያም ሆነ ይህ ሁሉም አካላት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በብሔራዊ ጉዳይ አብረው መነሳት እንዳለባቸው ይመከራል፡፡
ግብጻውያን በግድቡ ዙሪያ የሚሰጡትን ትኩረት በመመልከት ይህንን ለትውልድ የሚጠቅም ግድብ መከታተል የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነም ይነሳል፡፡