ውሳኔው የተላለፈባቸው ፓርቲዎች በፍርድ ቤት ክርክር ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የፓርቲ መሰረዝ ወይም መፍረስ ውጤትን አስመክቶ የተደነገገው አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን አስታወቀ።
ውሳኔው የተላለፈባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ኦሮሞ ኦቦ ነጻነት ግንባር ( ኦአነግ)፣ የኦሮሞ አንድነትና ዴሞክራሲ የፌዴራል የሰላም ለውጥ ( ኦአዴፌሰለ)፣ የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር ( ኦነአግ) እና ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ( ኦዳ) መሆናቸውን አስታውቋል
ቦርዱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ከዚህ ቀደም የቦርዱን ምዝገባ መስፈርት ያላሟሉ ከ27 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መሰረዙን አስታውሷል።
በህጉ መሰረትም በቦርዱ ውሳኔ ቅር የተሰኙ የተለያዩ ፓርቲዎች ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ ክርክር ሲያደርጉ መቆየታቸውን በመግለጫው አስታውቋል።
ፓርቲዎች ቦርዱ ላይ ባቀረቡት አቤቱታ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ቦርዱ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት የመሰማት መብት ለፓርቲዎቹ መስጠት ነበረበት በማለት ለፓርቲዎቹ የመሰማት መብት እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረትም ቦርዱ ለአራቱም ፓርቲዎች የመሰማት እድልን መስጠቱን እና ፓርቲዎቹም በተሰጣቸው እድል መሰረት ምላሻቸውን እንዳቀረቡ ገልጿል።
ሆኖም ግን የፓርቲዎቹ ዝቅተኛው ህጋዊ የአባላት ፊርማ 35 በመቶ በላይ መሆን ሲኖርበት አሁንም 35 በመቶ ህጋዊ መስራቾች ፊርማን አሟልተው አለማቅረባቸው በድጋሚ ማረጋገጡን አስታውቋል።
በዚህ መሰረት ፓርቲዎቹ ከምዝገባው ሂደት መውጣታቸውን እንዲሁም በአዋጅ 1162/2011 ዓ.ም በተደነገገው መሰረት የፓርቲ መሰረዝ ወይም መፍረስ ውጤትን አስመክቶ የተደነገገው ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን በመግለጫው አስታውቋል።