ምርጫ ቦርድ ኢዜማን ጨምሮ 6 ፓርቲዎች ምልክታቸውን እንዲቀይሩ ጥሪ አቀረበ
የቀደመ ምልክታቸውን ለመጠቀም የጠየቁ ፓርቲዎች መኖራቸውም በምክንያትነት ተቀምጧል
ፓርቲዎቹ ምልክቶቻቸውን እንዲቀይሩ የተጠየቁት ከዚህ በፊት በነበረው ምርጫ ሌሎች ፓርቲዎች ሲጠቀሙበት የነበረ እና የተመሳሰለ ምልክትን በማቅረባቸው ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ን ጨምሮ 6 ፓርቲዎች የምርጫ ምልክቶቻቸውን እንዲቀይሩ ጥሪ አቀረበ፡፡
“የተለያዩ” በሚል በቦርዱ በተጠቀሱ ምክንያቶች ምልክቶቻቸውን እንዲቀይሩ የተጠየቁት ፓርቲዎች የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ፣ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ፣ የምእራብ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያቂ ንቅናቄ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ናቸው፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ፣ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ኢዜማ የመረጡት ምልክት ከዚህ በፊት በነበረው ምርጫ ሌሎች ፓርቲዎች ሲጠቀሙበት የነበረ ነው፡፡ ፓርቲዎቹም የቀድሞ ምልክታቸውን ለመጠቀም ጠይቀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ቦርዱ ምልክቶቻቸውን እንዲቀይሩ እነ ኢዜማን የጠየቀው፡፡
የምእራብ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያቂ ንቅናቄ ፓርቲ ምልክቶች ደግሞ በሌሎች ፓርቲዎች ከቀረቡ ምልክቶች ጋር የተቀራረበ ምልክትን በማቅረባቸው ነው ተብሏል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ደግሞ ህጋዊ ሃላፊነት በተሰጠው አካል ምልክታቸውን እንዲመርጡ የተጠየቁ የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የምርጫ ምልክት በማስገባታቸው ነው፡፡
በመሆኑም የምርጫ ምልክቶቻቸውን ያላስገቡ፣ እንዲቀይሩ የተገለፀላቸው ወይም መቀየር የሚፈልጉ ፓርቲዎች እስከ ጥር 23 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ እንዲያጠናቅቁ ቦርዱ አሳስቧል፡፡
የጸደቁ ምልክቶችን እና የፓርቲዎችን ዝርዝር ሂደቱ ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚያደርግም ነው የገለጸው፡፡
ቦርዱ እስከአሁን 45 ያህል ፓርቲዎች ምልክቶቻቸው ማስገባታቸውን አስታውቋል።