የተሰረዙት ፖለቲካ ፓርቲዎች አዲሱን የምርጫ ቦርድ መስፈርት ያላሟሉ ናቸው
ምርጫ ቦርድ 27 ፓርቲዎችን ሰረዘ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲሱ ህግ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን አላሟሉም ያላቸውን 27 ፓርቲዎች መሰረዙን አስታውቋል፡፡
ፓርቲዎቹ በቀድሞ ህግ ሰርተፍኬት የነበራቸው እና ምዝገባ ጀምረው የነበሩ ናቸው፡፡
በአዲሱ ህግ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልተው እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ/ም ድረስ እንዲያቀርቡ ለ106 ፓርቲዎች ደብዳቤ ጽፌ ነበር ያለው ቦርዱ 76ቱ ብቻ ሰነዶችን ማቅረባቸውን ገልጿል፡፡
በፖለቲካ ፓርቲዎቹ የቀረበው ሰነድ በሕጉ መሠረት ተሟልቶ የቀረበ ስለመሆኑ እየተመረመረ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው፡፡
ስራው እንደተጠናቀቀም ከ76ቱ መካከል ምን ያህሉ መስፈርቱን እንዳሟሉ በቦርዱ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ነገር ግን የሚጠበቅባቸውን ሰነድ ማስገባት ያልቻሉ እና ጊዜ እንዲራዘምላቸው የጠየቁ 15 የፓለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ ከነዚህ ፓርቲዎች መካከል የ13ቱ አጥጋቢ ምክንያት ባለማቅረባቸው እንዲሰረዙ ቦርዱ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል ከቦርዱ በተደረገው ጥሪ መሰረት ሰነዶቻቸውን ያላቀረቡ እና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መዋሃዳቸውን የገለጹ ሌሎች 14 ፓርቲዎችም ተሰርዘዋል፡፡
የተጠየቁትን ሰነዶች ያላቀረቡ ሁለት ፓርቲዎች ማቅረብ ያልቻሉበት ምክንያት በፓርቲው የውስጥ ችግር የተነሳ መሆኑ ስለታመነበት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን የኮቪድ ወረርሽኝ በሚያበቃበት ወቅት እንዲያከናውኑ ቦርዱ ሲወስን ሌሎች ሰነዶቻቸው ግን ከላይ በተጠቀሰው መንገድ እየተገመገሙ ይገኛል፡፡
የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ሳያገኙ የተሰረዙ ፓርቲዎች
1. የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ
2. የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) -የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
3. የየም ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (የብዴን) -የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ
4. የደንጣ ዱባሞ ክችንችላ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት-የመስራች አባላት ዝርዝርም ያላቀረበ፣ ጉባኤ ያላካሄደ
5. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ (ኮንግረስ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
6. የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ( ትወብዴድ) - ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ
7. የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባኤም ያላካሄደ
8. የኢትዮጵያን አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ) - ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ
9. የመላው አማራ ህዝብ ፓርቲ (መዐሕፓ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
10. የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
11. የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ ( ደቡብ ኮንግረስ) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
12. የሸኮና አካባቢው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሸአሕዲድ) -ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄደ
13. ነጻነትና ሰላም ለኢትዮጵያ ህብረት ፓርቲ ( ነጻነትናሰላም) - የመስራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
ሰነድ ባለማምጣታቸው የተሰረዙ
1. የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ
2. መላው ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
3. የከምባታ ሕዝቦች ኮንግረስ
4. የሐድያ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
5. የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት
6. የዲል ወቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
7. የቤንች ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት
8. የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
9. የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ
10. የሱማሌ አንድነት ፓርቲ
11. ነፃነት ለአንድነትና ለፍትሕ ፓርቲ
12. ብሔራዊ ተሀድሶ ለሰላም ልማት
13. የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት
14. የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ
በልዩ ሁኔታ ሰነዶች እንዲታይላቸው የተደረጉ ፓርቲዎች
1. ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ( ኢዴፓ)
2. ወለኔ ህዝቦች ፓርቲ