የሟቹ አሚር ሳባህ የቀብር ሥነ-ስርዓት ዛሬ ተፈጽሟል
አዲሱ የኩዌት አሚር ናዋፍ አል ሳባህ በፓርላማ ቃለ መሃላ ፈፀሙ
ትናንት ህይወታቸው ባለፈው የኩዌት አሚር ሼክ ሳባህ አል አህመድ ምትክ ኩዌትን እንዲመሩ የተሰየሙት አዲሱ የሀገሪቱ አሚር ሼክ ናዋፍ አል ሳባህ ዛሬ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም ረቡዕ እኩለ ቀን ላይ በፓርላማው ቃለ መሃላ በመፈፀም የሀገሪቱ ተተኪ አሚር የመሆናቸውን ሂደት አጠናቀዋል፡፡
ትናንት ማክሰኞ በ 91 ዓመታቸው የሞቱት የሼክ ሳባህ ልዑል አልጋ ወራሽ የነበሩት ሼክ ናዋፍ በካቢኔው ማክሰኞ ምሽት ነው አዲስ መሪ ሆነው የተሰየሙት፡፡ የዛሬው የፓርላማው ቃለ መሐላ ደግሞ የ 83 ዓመቱን አዛውንት ወደ ዙፋን ጉዞ ፈጽሟል፡፡
አዲሱ ኤሚር "ህገ-መንግስቱን እና የሀገሪቱን ህጎች ለማክበር እና የህዝቦችን ነፃነት ፣ የገንዘብ እና ሌሎች ፍላጎቶች ለማስጠበቅ እንዲሁም የሀገሪቱን ነፃነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ እምላለሁ" ብለዋል ሼክ ናዋፍ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ፡፡
ፈታኝ ሁኔታዎችን በመጋፈጥ ለባህረ-ሰላጤው የአረብ ሀገራት ብልፅግና እና መረጋጋት ለመስራት አዲሱ አሚር ቃል ገብተዋል፡፡
ሼህ ናዋፍ በተሰበረ ድምጽ ባደረጉት ንግግር ሟቹ አሚር ሼክ ሳባህ ያከናወኗቸውን ስኬቶች እና ምክሮች በማስታወስ አክብሮታቸውን ገልጸዋል፡፡ "ኩዌት በታሪኳ ብዙ ቀውሶችን አሸንፋለች ዛሬ አንድነትና ከባድ ስራን የሚሹ ወሳኝ ፈተናዎች አጋጥሞናል" ማለታቸውን ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
በተያያዘ ዜና የሟቹ አሚር ሼክ ሳባህ አስከሬን ከአሜሪካ ወደ ኩዌት ተመልሶ የቀብር ሥነ ስርዓቱ ተፈጽሟል፡፡
አስከሬኑ ከአሜሪካ ሲመለስ አዲሱ አሚር በአየር ማረፊያ ተገኝተው ተቀብለዋል፡፡
የቀብር ሥነ ስርዓታቸውም የሀገሪቱ ባለስልጣናት እና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ነው የተፈጸመው፡፡