“የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በግብፅ የውሃ ድርሻ ላይ ምንም ጉዳት አያስከትልም” የሱዳን የቀድሞ የውሃ ሚኒስትር
የሱዳን የቀድሞ የውሃ ሚኒስትር ዑስማን አቱም (ዶ/ር) ከግድብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለ 49 ዓመታት ሰርተዋል
ሕዳሴ ግድብ በሱዳንና ግብፅ ላይ እንደሚያስከትል የሚጠቀሱ ጉዳቶች በአብዛኛው ስህተት መሆናቸውን ዶ/ር ዑስማን ገልጸዋል
የሕዳሴ ግድብ ሁለኛው ዙር የውኃ ሙሌት በግብፅ የውሃ ድርሻ ላይ “ምንም አይነት ጉዳት እንደማያስከትል” የቀድሞው የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስትር አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ዑስማን አቱም (ዶ/ር) ከስካይ ኒውስ አረቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለው የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ፣ በሁለተኛወም ይሁን በሦስተኛው ዙር ፣ ምንም አይነት ጉዳትና አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይኖረው አብራርተዋል፡፡
ከግድብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለ 49 ዓመታት መሥራታቸውንና እየሰሩም መሆናቸውን የገለጹት የቀድሞው ሚኒስትር ፣ ሁለተኛው እና ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት “ምንም ችግር አያስከትልም” ብለዋል፡፡ ይህ በስሌት የሚረጋገጥ እውነታ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ዑስማን መሃንዲሶች ጉዳዩን ይበልጥ በቀመር ሊያስረዱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ግድቡ ለታችኞቹ ተፋሰሶች የሚሰጣቸው ጥቅም ፣ ሊያደርስ ይችላል ከሚባለው ጉዳት ጋር ሊነጻጸር የሚችል እንዳልሆነም ነው ዶ/ር ዑስማን የሚገልጹት፡፡ ሱዳናዊው ምሁር እንደሚሉት በግድቡ ጉዳይ ለማብራራት ከሱዳን እና ከግብፅ በየሚዲያው የሚቀርቡ ግለሰቦች የዘርፉ ባለሙያዎች ቢሆኑ ስለግድቡ ትክክለኛ መረጃ መስጠት ይችሉ ነበር፡፡ ግድቡ ያስከትላቸዋል ተብለው የሚጠቀሱ ችግሮች በአብዛኛው ስህተት እንደሆኑ እና ጥቅሙ እጅግ እንደሚያመዝንም ነው የገለጹት፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ከመካከለኛ በላይ ከፍ ያለ የውሃ ፍሰት እና ጎርፍ እንደነበርም ዶ/ር ዑስማን አስታውሰዋል፡፡ በአስዋን ግድብ ውስጥ ባለፈው ዓመት ብቻ 24 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ መከማቸቱንም ነው የጠቆሙት፡፡
ኢትዮጵያ በሁለተኛው ዙር ሙሌት 13 ነጥብ 5 ፣ በሦስተኛው ዙር ደግሞ 10 ነጥብ 5 ሜትር ኪዩብ ውሃ ለመያዝ ማቀዷን ያነሱት የቀድሞው የሱዳን ካቢኔ አባል ፣ ይህ ሙሌት ግብፅ የውሃ ጉድለት እንዲገጥማት እንደማያደርግ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የቪክቶሪያ ሐይቅ የውሃ ይዘት ከፍ እያለ ስለመጣ የነጭ ዓባይ መጠንም እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡
ግብፅ በተደጋጋሚ ውሃው በሚያዝበት ጊዜ የውሃ ድርሻዬን ይቀንስብኛል በሚል አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ የግድቡ ሙሌት እንዳይከናወን የሚል አቋም በማንፀባረቅ ላይ ነች፡፡
ሕዳሴ ግድብ፣ ሱዳንና ግብፅ ድርቅ በሚያገጥማቸው ወቅት “በጣም ይጠቅማቸዋል” ያሉት ዶ/ር ዑስማን፣ ግድቡ የታቀደለትን የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ መካከለኛ የፍሰት መጠን የሚባለውን 48 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ ታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገሮች መልቀቅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በበሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እና አስተዳደር ላይ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ግብፅ ግድቡን ለማስተዳደር እና የዕለት ከዕለት የሥራ እንቅስቃሴውን ለማወቅ ግድቡ ባለበት ቦታ ቢሮ ለማቋቋም ላቀረበችው ጥያቄ የኢትዮጵያ ውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) “አስዋንን ግብፅ እንደምታስተዳድር ሁሉ ሕዳሴንም ኢትዮጵያ ታስተዳድራለች” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
የግድቡን ድርድር ዳግም ለማስጀመር የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኪንሻሳ ያደረጉት ውይይትም ፣ በቀጣይነት ማን ያደራድር በሚለው ጉዳይ ላይ መግባባት ሳይችሉ ያለውጤት ተጠናቋል፡፡ ሱዳን እና ግብጽ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ ከአፍሪካ ውጭ ያሉት አካላት ከታዛቢነት ያለፈ ሚና እንዲኖራቸው አትሻም፡፡