በግድቡ ጉዳይ ለ3 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኪንሻሳው የሶስትዮሽ ውይይት ያለስምምነት ተጠናቀቀ
በዴሞክራቲክ ሪፐብክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ በግድቡ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮች ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁን የሱዳንና የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች አስታውቀዋል፡፡
ነገርግን ኢትዮጵያ እስካሁን የኪንሻሳውን ወይይት በተመለከተ መግለጫ አላወጣችም፡፡
ሱዳን፣ ኢትዮጵያ በኪንሻሳው ውይይት ላይ “ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስቸግር ግትር አቋም አራምዳለች” ብላ ስትከስ, ግብፅ ደግሞ “ኢትዮጵያ ሁሉንም የድርድር ሂደት አማራጮች ውድቅ ማድረጓን” አስታውቃለች፡፡
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ አምባሳደር አህመድ ሀፌዝ “በኪንሻሳ የተካሄደው ውይይት ምንም መሻሻል አላሳየም፤ ድርድሩን ለመጀመርም ስምምነት ላይ አልተደረስም” ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ፣ በኪንሻሳ የሚመራና በአራት አካላት አደራዳሪነት ድርድሩ ይካሄድ የሚለውን በሱዳንና በግብፅ የቀረበ ሀሳብ ባለመቀበሏ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መቅረቱን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካና የአፍሪካ ህብረት በግድቡ ጉዳይ በአደራዳሪነት ይግቡ የሚለውን ሀሳብ እንደማትቀበል በውጭ ጉዳይ ሚኒቴሯ በኩል ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ሼሲኬዲ የሚመራው ውይይት ባለፈው ቅዳሜ በቴክኒክ ባለሙያዎች ስብሰባ ነበር የተጀመረው፡፡
ግብፅ እና ሱዳን ስምምነት ላይ ሳይደረስ የግድቡ ሁለተኛ ሙሌት እንዳይከናወን ቢጠይቁም የግድቡ የውሃ ሙሌት ከግንባታው ጋር የተያያዘ መሆኑን የምትገልጸው ኢትዮጵያ በቀጣዩ ክረምት ሙሊቱን ለማከናወን ዝግጅት በማድረግ ላይ ናት፡፡
በቅርቡ የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ “ከግብጽ ውሃ ማንም አንዲትም ጠብታ ሊነካ አይችልም ፤ ይህ ከሆነ ግን ማንም ሊያስበው የማይችል አለመረጋጋት በቀጣናው (ምስራቅ አፍሪካ) ይፈጠራል” በማለት መዛታቸው ይታወሳል፡፡
ነገርግን ኢትዮጵያ ግድቡ ለልማት ዓላማ ብቻ የሚውልና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ፣ ማለትም ግብፅና ሱዳን ፣ ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያስከትል በተደጋጋሚ ትገልጻለች፡፡