የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለሶስት ፕሮጀክቶች የሚውል የ907 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እና የዓለም ባንክ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚ/ር ኦስማን ዲዮን ተፈራርመዋል
ድጋፉ ለአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ፣ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት እና ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከል የሚውል ነው
የኢትዮጵያ መንግስት እና የዓለም ባንክ የ907 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ዛሬ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እና የዓለም ባንክ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚ/ር ኦስማን ዲዮን ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ ሶስት አንኳር ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚውል ሲሆን ፣ የመጀመሪያው የ200 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሚውል ነው፡፡
ሁለተኛው የ500 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በሀገሪቱ ለሚከናወነው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ካፒታል ተሳትፎን እና ዘላቂ የፋይናንስ አማራጮችን ለማምጣት ያለመ ነው፡፡ ከዚህ ስምምነት ውስጥ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ድጋፍ የሚውለው የግሉ ዘርፍ በኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ እና አቅርቦት ተሳትፎ እንዲኖረው ለማስቻል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡
ሦስተኛው የ207 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያስከተለውን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም የበሽታው መከላከያ ክትባቶች ውጤታማ እና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲዳረሱ ለማድረግ የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ ነው፡፡