የዓለም ባንክ ለ2025 የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት እቅድ የ500 ሚሊየን ዶላር ብድር አፀደቀ
ኢትዮጵያ በአሌክትሪክ አቅርቦት ዘርፍ አበረታች ለውጥ ብታመጣም ግማሽ የሚሆነው ህዝቧ ኤሌክትሪክ እንደማያገኝ ተገልጿል
ብድሩ ለ 5 ሚሊየን ህዝብ ፣ ለ11,500 ኢንተርፕራይዞች እና ለ 1,400 ቋማትና ኤሌክትሪክን ለማቅረብ ያለመ ነው
የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2025 አሌክትሪክን ሙሉ በሙሉ ለዜጎቿ ተደራሽ ለማድረግ የያዘችውን ግብ ማሳካት እንዲቻል አዲስ የብድር ማእቀፍ ማፅደቁን አስታውቋል።
የዓለም ባንክ በዓለም አቀፉ የልማት ማህበር (አይዲኤ) በኩል ለግቡ መሳካት የ500 ሚሊየን ዶላር ብድር ማፅደቁን ነው በድረ ገጹ የገለጸው፡፡
ባንኩ ብድሩን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት በአሌክትሪክ ተደራሽነት እና አቅርቦት ላይ አበረታች ለውጦችን ማምጣቷን አስታውቋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ ለሚሆኑ ዜጎቿ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ እንዳልቻለች ባንኩ ገልጿል።
በሀገሪቱ የኤልክትሪክ ተደራሽነት አለመስፋፋት ፣ የህዝቦቿ የድህነት ሁኔታ እንዲቀጥል፣ ዜጎች መሰረታዊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶቻቸውን እንዳያሳኩ እንዲሁም አማራጮችን እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑንም ባንኩ በመግለጫው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ የኤክትሪክ ብርሃን ተደራሽነት ፕሮጄክት የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮግራም ዋነኛ አካል እንደሆነ ያስታወቀው ባንኩ፣ ይህም በአውሮፓውያኑ 2025 አሌክትሪክን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ የማድረግ ግብን ለማሳካት እንደሚረዳ ጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ 5 ሚሊየን ለሚጠጋ ህዝብ፣ ለ11 ሺህ 500 ኢንተርፕራይዞች ፣ ለ 1 ሺህ 400 የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ኤሌክትሪክን ለማቅረብ ያለመ ነው።
ባንኩ የገንዘብ ብድር ያመቻቸለት ፖርጄክቱ በኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ኤልክትሪክ አግልግሎት እና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አማካኝነት የሚተገበር መሆኑንም አስታውቋል።