የ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ ንቅናቄ መሪ በየመን እስር ቤት ቃጠሎ የሞቱ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ ወደ ተመድ ሊወስድ እንደሚችል አስታወቀ
በሰንዓ የስደተኞች ማቆያ እስር ቤት ቃጠሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን መሞታቸው የሚታወስ ነው
የኢትዮጵያውያኑ ችግር ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን አላገኘም ያለው ኒውሰም ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ልንወስደው እንችላለንም ብሏል
በአሜሪካ የግሬተር ኒውዮርክ ከተማ የ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ ንቅናቄ መሪ ሃውክ ኒውሰም “የአፍሪካውያንን ችግር በተለይም በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ችግር ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ሊያቀርብ እንደሚችል” አስታወቀ፡፡
ኒውሰም ቀዳሚ የሚባሉ የአሜሪካ ብዙሃን መገናኛዎች “ለጥቁሮች በተለይም በየመን ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሚሰጡት አነስተኛ የዘገባ ሽፋን” መደንገጡን ተናግሯል፡፡
ኒውሰም ታዋቂው ጋዜጠኛ እና ኮሜዲ ሬይ ሃናንያ በአሜሪካ በሚሰራጨው የአረብ ሬዲዮ ኔትወርክ ላይ በሚያዘጋጀው የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ተገኝቶ ነው ይህን ያለው፡፡
በቆይታው “ሰዎች በግጭት ፖለቲካ ላይ ከማተኮር ይልቅ በአሜሪካ እና ከአሜሪካ ውጭ ስለሚገደሉ ጥቁሮች ሊቆረቆሩ” እንደሚገባ ተናግሯል እንደ አረብ ኒውስ ዘገባ፡፡
ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል ብሎ ያነሳውም ባሳለፍነው ወር የመን ሰንዓ ውስጥ በሚገኝ የሃውቲ ታጣቂዎች የስደተኞች ማቆያ እስር ቤት ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ የሞቱ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ ነው፡፡
በቃጠሎው በእስር ቤቱ የነበሩ 44 ኢትዮጵያውያን ህይወት አልፏል ብሏል ኒውሰም፡፡
“በግል የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የምጠመድበት ጊዜ የለኝም” ያለው ኒውሰም “በኢትዮጵያ ዜጎች ለግድያ እና ለጾታዊ ጥቃቶች እየተዳረጉ እንደሆነ አውቃለሁ” ብሏል፡፡
ሃውቲዎቹ በእነዚህ የሚያስጠጋቸውን በሚፈልጉ አፍሪካውያን ስደተኞች ላይ የፈጸሙትን “መስማቱ ልብ ይሰብራል”ም ነው ያለው፡፡
ከየትኛውም ፖለቲካዊ ጉዳይ በላይ የዜጎች ህይወት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግሯል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በገጠማቸው ማዘኑን የገለጸም ሲሆን ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
አረብ ኒውስ አማጽያኑ ኢንቲሳር አል-ሃማዲ የተባለች ኢትዮ-የመናዊ ሞዴል ማገታቸውንም በዝርዝር ዘገባው ጠቁሟል፡፡