“ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ ሙሌት በተያዘው ጊዜ እንደምናከናውን ለአሜሪካ ልዑክ ገልጸናል” አምባ. ዲና
ከሱዳን ጋር በተያያዘ “እኛ ከህዝቡ ጋር ችግር የለብንም ፤ ይህንን የሚያደርው ግን ወታደራዊ ክንፉ ነው” ብለዋል
ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ በተመለከተ በርካታ ሀገሮች ሽምግልና እየመጡ መሆኑን አምባ. ዲና ገልጸዋል
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘው ጊዜ ለማከናወን የጀመረችውን ስራ በምንም መልኩ እንደማታቋርጥ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ከሕዳሴ ግድብ እና ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ ያሉ አለመግባባቶችን በሰላም ለመፍታት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ለአሜሪካ ልዑክ መገለጹን ተናግረዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና “ለሁለተኛ ጊዜ የሕዳሴ ግድብን የመሙላት ሂደት (በቀጣይ ሀምሌ ወር የታቀደውን) እንደምናከናውን በሱዳን ለአሜሪካ መልዕክተኛ ዶናልድ ቡዝ አሳውቀናል” ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣ የሕዳሴ ግድብ ድርድሩን ሂደት ማስቀጠልን በተመለከተ ከአሜሪካ መልዕክተኛ ጋር የተሳካ ውይይት ማድረጋቸውን አምባሳደር ዲና ጠቁመዋል ፡፡
የድርድሩን መንገድ መቀየር ካስፈለገ በ2015 የመርሆች ስምምነት መሰረት መሆን እንዳለበትም ነው አቶ ደመቀ ለመልዕክተኛው ያብራሩት፡፡
በሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ ኢትዮጵያ ፣ ግብፅ እና ሱዳን ላለፉት 10 ዓመታት ያደረጉት ድርድር እስካሁን ውጤት ማምጣት አልቻለም፡፡
ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ የአሜሪካ ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት የተካተቱበት አራት አካላት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ ሹዳን ያቀረበችው ሀሳብ በግብፅ የተደገፈ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ውድቅ አድርጋዋለች፡፡
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ውጥረት በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ፣ “በርካታ ሀገሮች ከሱዳን ጋር ያለንን ነገር እንደትለውጡ ብለው ሽምግልና እየመጡ ነው” ያሉት አምባሳደር ዲና “እኛ ከህዝቡ ጋር ምንም ችግር የለብንም ፤ ይህንን የሚያደርው ግን ወታደራዊ ክንፉ ነው” ብለዋል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ውይይቶችና ግንኙነቶችን ለማድረግ መታቀዱንም ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ለረዥም ዓመታት የቆየ የድንበር ውዝግብ ቢኖርም ፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ ውጥረቱ አይሏል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ውጊያ ተከትሎ በቀናት ልዩነት ሱዳን አወዛጋቢውን የአል-ፋሻቃ አካባቢ መቆጣጠሯ ነው፡፡ አካባቢውን ሱዳን “በኢትዮጵያ የተያዘባት የግዛቷ አካል” አድርጋ ስትገልጽ ፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ በትግራይ የተፈጠረውን ችግር በመመርኮዝ “በሱዳን ወረራ እንደተፈጸመባት” ትገልጻለች፡፡ ሱዳን ከያዘችው ቦታ ለቃ ካልወጣች ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ከሱዳን ጋር ለድርድር እንደማትቀመጥ አቋም ይዛለች፡፡