የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ የሚተኛበት ስፍራ የደን ምንጣሮ ሊጀመር ነው
በሁለተኛው ዙር በ4 ሺህ 854 ሄክታር ቦታ ላይ የሚገኝ ደን ይመነጠራል ተብሏል
በቀጣይ ክረምት ውሃ ለሚተኛበት ቦታ የደን ምንጣሮ ለማከናወን በአሶሳ ከተማ የሳይት ርክክብ ተካሂዷል
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ ሁለተኛ ዙር የደን ምንጣሮ ለማከናወን ዛሬ በአሶሳ ከተማ የሳይት ርክክብ ተካሄደ፡፡
ርክክቡን ያካሄዱት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቴክኒክ ሙያና ስራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የኢንቫይሮመንታል እና ሶሻል ፕላኒንግ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ፣ ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በመጪው ክረምት እንደሚካሔድ በርክክቡ ወቅቱ ተናግረዋል፡፡
ውሃው የሚተኛበት ቦታ ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን ሲሆን ከዚህ ውስጥ በሁለተኛው ዙር በስፍራው በ4 ሺህ 854 ሄክታር ላይ የሚገኝ ደን እንደሚመነጠርም ገልጸዋል፡፡ ስራው በጂ.ፒ.ኤስ. በታገዘ ካርታ እንደሚከናወንም ነው የገለጹት፡፡
ስራው ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተው “የአካባቢውን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ስራውን በወቅቱ እናጠናቅቃለን” ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቴክኒክ ሙያ እና ስራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም በበኩላቸው ስራውን ለማከናወን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ስራውን የሚያከናውኑ ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ስራ አጥ ወጣቶች በኢንተርፕራይዝ እንዲደራጁ መደረጉንም አቶ በሽር አስታውቀዋል፡፡
ለደን ምንጣሮ ስራው ከ81 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንና ከአምስት ሺህ በላይ የስራ እድል እንደሚፈጥር የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የመጀመሪያ ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት ከመካሄዱ አስቀድሞ በስፍራው የሚገኝ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ ደን ምንጣሮ ስራ መከናወኑ ይታወሳል፡፡