በህንድ ገበያ የደራላቸው "የሌብነት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶች"
ትምህርት ቤቶቹ አንድ “ጥሩ ሌባ” አሰልጥኖ ለማውጣት እስከ 300 ሺህ ሩፒ ድረስ ያስከፍላሉ

ፖሊስ ትምህርት ቤቶቹን ለመዝጋት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ማህበረሰቡ በሚያደርግላቸው ከፍተኛ ጥበቃ ምክንያት ሊሳካ አልቻለም
በህንድ ሶስት ገጠራማ መንደሮች የሚገኙት "የሌባ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶች" ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ይገኛል፡፡
መገኛቸውን ማድያ ፕራዴሽ በተባለ ክልል የገጠር አካባቢዎች ውስጥ ያደረጉት ሶስት ትምህርት ቤቶች በዋናነት የሚያሰለጥኑት ከ12 አመት በታች የሚገኙ ህጻናትን ነው ተብሏል፡፡
ህጻናቱ በኪስ ማውለቅ፣ በመመንተፍ ፣ በስርቆት እና ዝርፍያን በመሳሰሉ ወንጀሎች ልምድ ባላቸው ወንጀለኞች ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
ትምህርት ቤቶቹ ሌብነትን ለማሰልጠን ከህጻናቱ ወላጆች ከ200 – 300 ሺህ ሩፒ ወይም ከ2400 – 3600 ዶላር ድረስ ክፍያ እንደሚቀበሉ ነው ኦዲቲ ሴንትራል ያስነበበው፡፡
አሰልጣኞቹ ከተለመዱ የስርቆት አይነቶች ባለፈ እንደ ሰልጣኞቹ የአዕምሮ ፍጥነት ደረጃ ባንክን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን የሚያጭበረብሩበትን መንገድ የሚያስተምሩ ሲሆን፤ በተጨማሪም በፖሊስ በሚያዙበት ወቅት የሚደርስባቸውን ድብደባ እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ ስልጠና እንደሚወስዱም ተሰምቷል፡፡
ህጻናቱ ምንም እንኳን ከደሀ ቤተሰብ የተገኙ ቢሆንም ሰርግ እና ትላልቅ ማህበራዊ መሰባሰቦች ላይ እራሳቸውን አመሳስለው ከቦርሳ እሰከ ወርቅ ጌጣጌጥ አንዳንድ ጊዜም የተደራጀ የዝርፍያ ወንጀል እንደሚፈጽሙ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በህንድ ስመ ጥር ሌቦችን በማሰለጠን ውጤታማ ናቸው የተባሉት እነኚህ የሌብነት ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ በድህነት ውስጥ በሚገኙ እና አቅመ ደካማ ወላጆች ዘንድ ተፈላጊነታቸው ጨምሯል ነው የተባለው፡፡
ህጻናቱ ለአንድ አመት ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የወንጀል ቡድኖችን ሲቀላቀሉ የወንጀል ቡድኖቹ በአመት ከ300 – 500 ሺህ ሩፒ ወይም 6 ሺህ ዶላር ድረስ ለህጻናቱ ወላጆች ይሰጣሉ፡፡
ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋባቸው በእነኚህ የገጠር መንደሮች ፖሊስ ስለ ወንጀል ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶቹ እውቅና ቢኖረውም ማህበረሰቡ ለአሰልጣኞቹ እና ትምህርት ቤቶች በሚሰጠው ከለላ ፖሊስ እርምጃ መውሰድ ተስኖታል፡፡
እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ ከነዚህ ትምህርት ቤቶች የወጡ 2ሺህ ሌቦች ከ8 ሺህ በላይ ወንጀሎች በስማቸው ተመዝግቦ ይገኛል፡፡