ኤክስፖው ላይ ኢትዮጽያን ጨምሮ የ192 ሀገራት የሚሳተፉበት ሲሆን፤ ከ25 ሚልየን በላይ ጎብኚዎች ይጠበቃሉ
በዱባይ ኤክስፖ 2020 መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ መካፈል ለሚፈልጉ ዓለም አቀፍ ታዳሚዎች የትኬት ሽያጭ መጀመሩ ተገለፀ።
የትኬት ሽያጩ እንደ አውሮፓውያ አቆጣጠር እስከ ነሃሴ 14 2021 የሚቆይ መሆኑንም የኤክስፖው አዘጋጆች አስታውቀዋል።
ከትኬት ሽያጩ በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች የነጻ መግቢያ የሎተሪ እድሎች መዘጋጀታቸውም ታውቋል።
እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ እና የግል አሊያም የቤተሰብ ትኬት እንደ አውሮፓውያ አቆጣጠር ከነሃሴ 14 2021 በፊት ትኬት የቆረጠ ማንኛውም ሰው በእጣው ውስጥ እንደሚካተት ተነግሯል።
የእጣው አሸናፊ 50 ሰዎችም በመስከረም ወር የመጀመሪያው ሳምንት ላይ በዱባይ ኤክስፖ 2020 የማህበራ ትስስር ድረ ገጾች ላይ ይፋ እንደሚደረጉም ታውቋል።
የዱባይ ኤክስፖ 2020 መክፈቻ ስነ ስርዓት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 20 2021 እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።
የዱባይ ኤክስፖ 2020 ላይ ኢትዮጽያን ጨምሮ የ192 ሀገራት እንደሚሳተፉበት የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከ25 ሚልየን በላይ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙትም ይጠበቃል።
የዱባይ 2020 ኤክስፖ ከጥቅምት እስከ መጋቢት 2013 ዓ.ም ለስድስት ወራት እንደሚካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፤ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ መራዘሙም ይታወሳል።
በአረብ ሀገራት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ ለተነገረለት የዱባይ ኤክስፖ 2020 ከ10 ዓመት በላይ ፈጀ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።