የእሳት አደጋ በ40 ደቂቃ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀገሪቱ ባለባለስልጣናት አስታውቀዋል
በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በጀበል አሊ ወደብ አቅራቢያ ዕቃ ጭኖ የቆመ መርከብ ውስጥ የደረሰው እሳት አደጋ በ40 ደቂቃ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀገሪቱ ባለባለስልጣናት አስታወቁ፡፡
በዱባይ መርከብ ላይ ተጭኖ በነበረ ኮንቴይነር በተከሰተ ከፍተኛ ፍንዳታ ለ40 ደቂቃ የተቀጣጠለውን እሳት አሁን ላይ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉ ተገልጿል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በሰው ላይ የደረሰ አደጋ አለመኖሩን የዱባይ መንግስት የሚዲያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ገልጸዋል።
ዳይሬክተሯ ሙና አልመሪ፤ መርከቧ የጫነችው ኮንቴይነር ተቀጣጣይ ነገር በውስጡ እንደነበረ ለአል ዐይን አስረድተዋል።
የዱባይ ሲቪል መከላከያ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ራሺድ ታኒ አል ማትሮሺ በበኩላቸው የእሳት አደጋው በአጋጣሚ የተከሰተ መሆኑንና ሞትም ሆነ የአካል ጉዳት እንደሌለ አረጋግጠዋል።
በኮንቴይነር ውስጥ ተጭኖ የነበረው ተቀጣጣይ ዕቃም ከፍተኛ አደጋ የሚያደርስ እንዳልነበረም ተናግረዋል። አክለውም ጀበል አሊ ወደብም ወደ መደበኛ ሥራው መመለሱ ተገልጿል።
የዱባይ ፖሊስ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አብደላህ አል ማሪ እንደገለጹት እሳት የተነሳባት መርከብ 130 ኮንቴይነሮችን የመያዝ አቅም ያላት ትንሽ የኮንቴነር መርከብ መሆኗ ተናግረዋል።