ቻይና ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳ የጸረ-ወረርሽኝ ኤክስፐርት ቡድን ወደ ጣሊያን ላከች
ቻይና ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳ የጸረ-ወረርሽኝ ኤክስፐርት ቡድን ወደ ጣሊያን ላከች
ከቻይና ቀጥሎ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ የተጠቃችው አውሮፓዊት ሀገር ጣሊያን ቫይረሱን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት የሚደግፉ 9 አባላት ያሉት የጸረ-ወረርሽኝ ኤክስፐርት ቡድን ዛሬ ከቻይና ሻንግሀይ በመነሳት ወደ ጣሊያን አምርቷል፡፡
31 ቶን የህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ ኤክስፐርቶችን የያዘው አውሮፕላን ከሻንግሀይ ፑዶንግ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዛሬ ሀሙስ መጋቢት 03 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ተነስቷል፡፡
ሲጂቲኤን እንደዘገበው በቻይና ቀይ መስቀል ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት የተመራው ቡድኑ ከሲቹአን ግዛት የተቀላቀሉ ተጨማሪ 5 ኤክስፐርቶችንም በጉዞው አካቷል፡፡
የቻይና ኤክስፐርቶች በሽተኞችን በማከም ረገድ ልምዳቸውን በማጋራት ጣሊያንን እንደሚያግዙ ነው የተገለጸው፡፡
ከቡድኑ አባላት አንዱ የሆኑት ሊያንግ ዞንግ በጣሊያን የቫይረሱ ሟቾች ቁጥር በተለይም እድሜያቸው በገፋ ታማሚዎች ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ “የጣሊያን የጤና ስርዓት ከኛ የተለየ ቢሆንም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎች በሚያስፈልጉበት ጊዜ ግን ተመሳሳይነት ስለሚኖረው የምንችለውን ድጋፍ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
“ቫይረሱ ሲከሰት ወደ ዉሀን ስንላክ ከነበረው በተሻለ አሁን ቫይረሱን ለመዋጋት ዝግጁ ነኝ” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የቫይረሱ መነሻና ዋነኛ ተጠቂ በሆነችው ቻይና እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙ 80952 ተጠቂዎች 63000 ያክል የሚሆኑት አገግመው ከሆስፒታል ወጥተዋል፡፡ በሀገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችም ቁጥር በከፍተኛ መጠን በመቀነስ ላይ ይገኛል፡፡
የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ በሚገኝባት ጣሊያን እስካሁን የተጠቂዎች ቁጥር ከ12,000 በላይ ሲደርስ የሟቾቹ ደግሞ 827 ደርሷል፡፡
ዛሬ ኮሮና ቫይረስ ዓለማቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ በዓለም ጤና ድርጅት ከታወጀ በኋላ ጣሊያን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል ከምግብ ቤቶች እና ፋርሲዎች ውጭ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ ወስናለች፡፡