ማዕቀቡ በጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሀንስ ላይ ያነጣጠረ ነው
አሜሪካ የኤርትራ ጦር በትግራይ ክልል ፈጽሟል ባለችው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት በጦሩ ዋና አዛዥ ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታወቀች።
ማዕቀቡ በኤርትራ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሀንስ ላይ የተጣለ ነው፡፡
ማዕቀቡን የተጣለው በአሜሪካ የፌዴራል ግምጃ ቤት (ትሬዠሪ) በኩል ሲሆን አዛዡ በአሜሪካ ያላቸው ሀብት እንዲታገድ እንደተወሰነ ግምጃ ቤቱ በድረገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
አሜሪካ በጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሀንስ የሚመራው የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሟል፤ ሴቶችን ደፍሯል እንዲሁም ወጣቶችን እና ንጹሀን ዜጎችን ቤት ለቤት በመግባት ገድሏል ስትል ከሳለች።
የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ካደረገ በኋላም ተመልሶ ወደ ትግራይ ክልል ገብቷል የሚለው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ጦሩ በአስቸኳይ ወደ ኤርትራ እንዲመለስ ጠይቋል።
ውሳኔው አሜሪካ ለሰብአዊ መብት ጥበቃ ላላት ቁርጠኝነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ነው ግምጃ ቤቱ ያስታወቀው።
አሁንም ጦርነቱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው የሚለው የህ ተቋም በቀጠለው ግጭት ምክንያት እርዳታ የሰብአዊ መብት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ማድረስ ባለመቻሉ ሁሉም አካላት ግጭቱን እንዲያስቆሙ ጠይቋል።
ኤርትራ ማዕቀቡን በተመለከተ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የሰጠችው ምላሽ የለም፡፡