የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ኤርትራውያን ስደተኞችን እና የትግራይ ተፈናቃዮችን ለመርዳት 164.5 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል አለ
የግጭቱ ተሳታፊ ኃይሎች የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ህጎችን በማክበር የንጹሃንን ደህንነት እንዲጠብቁም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል
ኮሚሽኑ ገንዘቡ ለ96 ሺ ኤርትራውያን ስደተኞች፣ ለ650 ሺ የትግራይ ተፈናቃዮች እንዲሁም በምስራቃዊ ሱዳን ለሚገኙ 120 ሺ ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች የሚውል ነው ብሏል
የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን /UNHCR/ ስደተኞችን ለመርዳት 164.5 ሚሊዮን ዶላር ጠየቀ፡፡
የስደተኞች ኤጀንሲ ገንዘቡን የጠየቀው 96 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች፣ 650 ሺህ በትግራይ ክልል ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች እንዲሁም 120 ሺህ የሚሆኑ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለመርዳት እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡
የእርዳታው 61 በመቶ ማለትም 101.3 ሚልዮን ዶላሩ መጠለያ ጣብያዎች ለመገንባት፣ አስፈላጊ ቁሳቁሶች ለማቅረብ እና በትግራይ ግጭት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመርዳት የሚውል መሆኑንም ነው የገለጸው ኤጀንሲው፡፡
63.2 ሚልዮን ዶላሩ በሱዳን ለሚገኙ ስደተኞች የተለያዩ የመጠለያ፣ ውሃ፣ ጤና እና ሎጂስቲክስ አቅርቦቶች የሚውል እንደሆነም ጭምር፡፡
ኤጀንሲው በሱዳን የሚገኙትን ስደተኞች በተመለከተ ባለፈው ወር ብቻ 40 ኤርትራውያንን ያካተቱ 275 ስደተኞች ወደ ሱዳኑ “ሃምዳይት መጠለያ ጣብያ” መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
900 የሚሆኑ የቅማንት ተወላጆች ከአማራ ክልል በጋላባት በኩል ወደ ሱዳን መዝለቃቸውንና ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጭምር ነው የገለጹት፡፡
ኤጀንሲው በመጨረሻም ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ኃይሎች የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ህጎች በማክበር የንጹሃንን ደህንነት እንዲጠብቁና ያልተገደበ እርዳታ እንቅስቃሴ እንዲኖር ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ጠይቋል፡፡