በትግራይ ጦርነት የህወሓት መሪዎችን ትደግፋለች በሚል ኤርትራ አሜሪካን ከሰሰች
ኤርትራ ለተመድ እንዳስታወቀችው “የእነዚህ ድርጊቶች ግልፅ ዓላማ የህወሓትን አገዛዝ ቅሪቶች እንደገና ለማደስ ነው”
ኤርትራ የባይደን አስተዳደር በቀጣናው ጣልቃ በመግባትና በማስፈራራት “ተጨማሪ ግጭቶችን እና አለመረጋጋትን እያስከተለ ነው” ብላለች
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላለፉት 20 ዓመታት ህወሓትን የደገፉት የአሜሪካ አስተዳደሮች በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ለተፈጠረው ጦርነት ተጠያቂ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ ኡስማን ሳሌህ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ ፣ ኤርትራን በጦርነቱ መወንጀል መሠረተ ቢስ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ኡስማን ሳሌህ በደብዳቤያቸው ላይ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ፣ በቀጣናው ጣልቃ በመግባት እና በማስፈራራት “ተጨማሪ ግጭቶችን እና አለመረጋጋትን እያስከተለ ነው” ሲሉ ከሰዋል፡፡ “የእነዚህ ድርጊቶች ግልፅ ዓላማ የህወሓትን አገዛዝ ቅሪቶች እንደገና ለማደስ ነው” ብለዋል፡፡
የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳሌህ “የህወሓት ቡድን እራሱን ለማስታጠቅ እና የአብይን መንግስት ለማሽመድመድ የሚያደርጋቸውን ህገ-ወጥ እቅዶቹን ለመሸሸግ የተሳሳተመረጃ በማሰራጨት ላይ መሆኑን” በመግለጽ የፀጥታው ምክር ቤት “ኢ-ፍትሃዊነትን ለማስተካከል ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወስድ” አሳስበዋል፡፡
ኡስማን ሳሌህ ፣ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግስት እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ላይ የጣለውን የቪዛ እገዳም ተቸተዋል፡፡ ውሳኔውን “በአንድ ወገን ብቻ የተፈፀመ የማስፈራራት እና ጣልቃ ገብነቶች” የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የኤርትራ ወታደሮችም በተሳተፉበት የትግራይ ክልል ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡበት ይነገራል፡፡ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ያሳሰበው የትራምፕ አስተዳደር ለግጭቱ መቀስቀስ ተጠያቂ ናቸው ባላቸው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የቀድሞ እና የአሁን ባለስልጣናት እንዲሁም ወታደራዊ አመራሮች ላይ የቪዛ እገዳም ጥሏል፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት አመራሮችም የቪዛ እገዳው አካል ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ፣ ለሕወሓት የጦር መሳሪያ የሚያቀብሉ በርካታ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ስለመኖራቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡