ግብጽ፣ ሳኡዲ አረቢያ እና ኢራን ጣፋጩን ፍራፍሬ በማምረት ቀዳሚ ሲሆኑ እስራኤል ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ታገኝበታለች
የረመዳን ወር ላይ ከማዕድ የማይጠፋው ቴምር በመካከለኛው ምስራቅ የተከበረ እንግዳ መቀበያ፤ በሰርግና በሀዘን ቤትም የማይጠፋ ፍራፍሬ ነው።
በርካቶች በአይረን፣ ፖታሲየም፣ ፕሮቲን፣ ፋይበር፣ ካልሲየም እና ቫይታሚኖች የተሞላውን ቴምር ጾም መግደፊያ ማድረጋቸውም የጤና በረከቶቹን ከመገንዘብ ይመስላል።
ጥቅሙን የተረዱ ሀገራትም ቴምርን በብዛት በማምረት ከጾም መግደፊያነት እና እንግዳ መቀበያነት በዘለለ ለውጭ ገበያ ያቀርቡታል።
በ2022 ብቻ 9 ነጥብ 91 ሚሊየን ቶን ቴምር መመረቱን የሚጠቅሰው የመንግስታቱ ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ምርቱ በየአመቱ እያደገ መሄዱን ይገልጻል።
ግብጽ 1 ነጥብ 73 ሚሊየን ቶን ቴምር በማምረት በአለማችን ቀዳሚዋ ሀገር መሆኗንም በማከል።
ጣፋጩን ፍራፍሬ በማምረት ቀዳሚ ከሆኑ 10 ሀገራት ስምንቱ የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ናቸው።
እስራኤልም በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆነ የቴምር አይነትን በማምረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ታገኛለች።
በዚህ አመት ግን በጋዛው ጦርነት ምክንያት በርካታ ሀገራት ከቴል አቪቭ ቴምር ላለማስገባት ወስነዋል።