ፆም ከመንፈሳዊ ፋይዳው ባሻገር በርካታ የጤና በረከቶች አሉት
ጾም መልካም ነገሮችን በመከወንና ከምግብ በመራቅ ከፈጣሪ በረከት የሚገኝበት እንደሆነ ይታመናል።
መጾም ከመንፈሳዊ ፋይዳው ባሻገር የጤና በረከቱ የበዛ መሆኑን በርካታ ጥናቶች አሳይተዋል።
በቅርቡም በ”ኔቸር ሜታቦሊዝም” የወጣ ጥናትም ሰውነታችን በጾም ወቅት የሚያስተናግዳቸው ለውጦች እና በዚህም የሚገኘውን ጥቅም አመላክቷል።
በግብጹ አሱይት ዩኒቨርሲቲ የስርአተ ምግብ ተመራማሪው ሞሀመድ ሻውካት ለአል አይን ኒውስ እንደተናገሩት፥ ጥቂት ምግብ መመገብ የምግብ መፈጨት ሂደት የሚከውኑ የሰውነት አካላት ስራ ይቀንሳል።
ይህም ሰውነታችን ለረጅም ጊዜ ያጣውን እረፍት እንዲያገኝ ያደርገዋል።
ለምግብ መፈጨት የሚያግዙ ኢንዛይሞችም ሰውነታችን ከተለያዩ ችግሮች ለመታደግ እንዲውሉ ያደርጋል ነው የሚሉት ተመራማሪው።
“ጾም ሰውነታችን እንዳዲስ ራሱን እንዲያደራጅ፤ ከድካም እንዲወጣና ጉልበት እንዲቆጥብ ያደርጋል”ም ብለዋል።
ሰውነታችን በጾም ስአታት ምን ለውጥ ያስተናግዳል?
ከ0 እስከ 4 ስአት
በዚህ ስአት ሰውነታችን ከመጨረሻው ምግብ የተገኘውን ሃይል ህዋሳትና ቲሹዎች ይሰራበታል፤ ይህም ግሉኮስን በመጠቀም መንቀሳቀስ እንድንችል ያደርጋል።
ከ4 እስከ 6 ስአት
በዚህ ወቅት ሰውነታችን ከመጨረሻ ምግባችን የተራረፈን ንጥረነገር አሟጦ ተጠቀሞ ሃይል የሚሰራበት ነው። ሃይሉ ጥቅም ላይ ውሎ ሲያልቅም ሰውነታችን የተከማቸ ስብን ወደ ሃይል ወደመለወጥ ይገባል።
ስብን በማቃጠል ሂደት የሚለቀቀው ኬቶን የተባለ ኬሚካል ሰውነታችን በሃይል እንዲሞላ ያደርጋል።
በሰውነት ህዋሳት ውስጥ የሚሞቱና እንደ እርጅና፣ ካንሰር እና ሌሎች በሽታዎች የሚያስከትሉ ነገሮች የሚወገዱትም ከጾምን ከ4 እስከ 6 ስአት ውስጥ ነው።
ከ16 ስአት በኋላ
ሰውነታችን ምግብ ካገኘ ከ16 ስአት በኋላ በህዋሳት ውስጥ የሚገኝ ግሉኮስ እና በጡንቻ ውስጥ የሚገኝ ግላይኮጂን በፍጥነት እንዲቀንስ ያደርገዋል። በዚህም የተከማቸ ስብን ወደመጠቀም ይገባል፤ ሂደቱም ሰውነታችን በአዲስ ሀይል እንዲሞላ ያደርጋል።
ምንም እንኳን በሰውነታችን ውስጥ ልዩ ለውጥ ቢኖርም በወጭ የሚታይ ነገር የለም፤ መንቀሳቀስም ሆነ ከሰዎች ጋር ማውራትም አያስቸግርም።