ታዋቂው ዩቲዩበር ሚስተር ቢስት ቲክቶክን ለመግዛት ጥያቄ አቀረበ
ቲክቶክ በአሜሪካ የሚሰጠው አገልግሎት በ4 ቀናት ውስጥ ሊቋረጥ መሆኑን ተከትሎ የተለያዩ ባለሀብቶች አገልግሎቱን ለመግዛት ጥያቄ እያቀረቡ ነው
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት ውሳኔውን ለመሻር ጣልቃ ካልገባ ቲክቶክ ትራምፕ ሊሾሙ አንድ ቀን ሲቀራቸው በመላ ሀገሪቱ አገልግሎት መስጠት ያቆማል
በዩቲዩብ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ከፍተኛ ተከታዮች በማፍራ በአለም ላይ ቀዳሚ የሆነው ጂሚ ዶናልድሰን (ሚስተር ቢስት) ቲክቶክን ለመግዛት ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ከአሜሪካውያን የግል መረጃ አያያዝ ጋር በተገናኘ በቀረበበት ክስ የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ አካል የሆነው ቲክቶክ በአሜሪካ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲሸጥ፤ የማይሸጥ ከሆነ ደግሞ በሀገሪቱ እንዲታገድ ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡
በኩባንያው ላይ በጆ ባይደን አስተዳደር ያወጣውን አዋጅ በመቃወም በፍርድቤት ሲከራከር የነበረው ኩባንያው በፍርድ ቤት ተሸንፎ በ4 ቀናት ውስጥ አገልግሎቱ ሊቋረጥ እንደሚችል እየተጠበቀ ነው፡፡
ከ340 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን በዩቲዩብ በማፍራት አለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን የቻለው ሚስተር ቢስት የኩባንያውን ግዢ አዋጪነት በተመለከተ ከአድናቂዎቹ እና ከሌሎች ተፅእኖ ፈጣሪዎች ጋር እየተመካከረ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
"ቲክቶክን ከመታገድ ለመታደግ ለመግዛት እያሰብኩ ነው፤ ይህን ሀሳብ በተመለከተ በኤክስ ላይ ሀሳቤን ካጋራሁ ጀምሮ ብዙ ቢሊየነሮች ሊያግዙኝ እንደሚፈልጉ ሀሳባቸውን እየገለጹልኝ ነው” ብሏል፡፡
የዩቲዩበሩ ብዙ ወዳጆቹ ከእንዲህ አይነቱ ግዙፍ ስምምነት ጋር አብረው የሚመጡትን ጠንካራ የገንዘብ እና የቁጥጥር ፈተናዎችን ሊጋፈጥ እንደሚችል እያስጠነቀቁት እንደሚገኙም ተናግሯል፡፡
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህጉን ተግባራዊነት ለመሻር ወይም ለማዘግየት ጣልቃ ካልገባ በስተቀር ቲክቶክ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሊሾሙ አንድ ቀን ሲቀረው በሀገር አቀፍ ደረጃ እገዳ ተጋርጦበታል፡፡
ከሚስተር ቢስት ባለፈ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብት ኢለን መስክ ከኩባንያው አገልግሎት ግዢ ጋር በተገናኝ ስሙ እየተያዘ ሲሆን ቲክቶክ ከጊዢው ጋር ተያይዞ ለቀረቡለት ጥያቄዎች “ለልቦለድ ፈጠራዎች መልስ አለስጠም” ሲል ተናግሯል፡፡
ሚስትር ቢስት ከዩቲዩብ ባለፈ በቲክቶክ ላይ ከ106 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን በመያዝ ከመድረኩ ታዋቂ ተጽኖ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ ነው።
የቲክቶክ ግዢ ሀሳቡን ካጋራ በኋላ እሱ ኢለን መስክ ወይም ሌላ ታዋቂ የአሜሪካ ስራ ፈጣሪ ቲክቶክን ለማዳን የባለሀብቶችን ቡድን ማሰባሰብ ይችሉ ይሆን የሚል ጥያቄን አጭሯል፡፡