ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ዋናው የፀሐይ ግርዶሽ የሚከሰተው ከ 140 ዓመታት በኋላ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የፀሐይ ግርዶሽ ታይቷል
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የፀሐይ ግርዶሽ የታየ ሲሆን እስከ እኩለቀን በተለያዩ አካባቢዎች ክስተቱ እንደሚኖርም ይጠበቃል፡፡
ዛሬ እሁድ ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ፀሐይ ከ60 እስከ 80 በመቶ ተሸፍና ከፊል ግርዶሽ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት መግለጹ ይታወቃል፡፡
ከ80 በመቶ በላይ ፀሐይ ተጋርዳ የምትታይበት ዋናው ግርዶሽ ደግሞ ከምዕራብ ኢትዮጵያ አንሥቶ እስከ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚገኙ ቦታዎች ጎልቶ እንደሚታይ ኢኒስቲዩቱ አስታውቋል፡፡
ክስተቱ ከወለጋ አካባቢ ጀምሮ ከፊል ጎጃም እና ከፊል ጎንደርን አልፎ ከዚያም ላሊበላን አቋርጦ ይሄዳል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ፀሐይ እስክ 99 በመቶ ተሸፍና ቀለበታዊውን ግርዶሽ ማየት እንደሚቻል ነበር ኢኒስቲዩቱ ያስታወቀው፡፡
ቀለበታዊ ግርዶሽ ማየት ከሚችሉ ስፍራዎች መካከል ቡሬ፣ አገው ግምጃ ቤት፣ እንጅባራ፣ ግሽ አባይ፣ ሞጣ፣ ዳሞት፣ ጋይንት፣ ነፋስ መውጫ፣ ጋሸና፣ ሙጃ፣ ዋጃ፣ ቆቦ፣ ኮረም፣ አላማጣ፣ ጊራራ እና ላሊበላ ይገኙበታል፡፡
በአዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ቤጊ፣ ሜቲ፣ መንዲ፣ ጫልቱ፣ በመሳሰሉት ከተሞች ደግሞ ቀለበታዊ ግረዶሽ ባይኖርም ከፊል የፀሐይ ግርዶሽ የታየባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡
ከማለዳ ጀምሮ በላሊበላ እና በአፋራ አካባቢም በተለያዩ ሰዓታት ላይ ሙሉ ቀለበቱ ታይቷል።
ይህን የፀሐይ ግርዶሽ ለመመልከት ከዓለም ላሊበላ አመቺ ስፍራ የነበረ በመሆኑ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተመራማሪዎች እና ጎብኚዎች ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የተመዘገቡ ቢሆንም ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መምጣት እንዳልቻሉ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿለ። ይሁንና ከወረርሽኙ በፊት ከውጭ ሀገራት የመጡትን ጎብኚዎች ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያንም በስፍራው ተገኝተው ክስተቱን ተመልክተዋል፡፡
በትግራይ ክልል አላማጣ ከተማም እንደ ላሊበላ ሁሉ ቀለበታማ (እሳታማ ቀለበት) የፀሐይ ግርዶሽ ተስተውሏል፡፡
የፀሐይ ግርዶሽ በአላማጣ -ምስል ከትግራይ ቲቪ
አላማጣ ከተማ በፀሐይ ግርዶሽ ወቅት -ምስል ከትግራይ ቲቪ
በባሕር ዳር ፣ እንጅባራ እና የተለያዩ አካባቢዎችም ክስተቱ ጎላ ብሎ መታየቱን ከተለያዩ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በዓለማችን ምስራቃዊ ንፍቀ ክበብ መቢገኙ አንዳንድ ሀገራትም የፀሐይ ግርዶሽ ተስተውሏል፡፡ የአፍሪካ መካከለኛው አካባቢ ፣ ደቡባዊ የዓረብ ባህረ ሰላጤ ፣ ፓኪስታን ፣ ሰሜናዊ ህንድ እና ደቡብ ማዕከላዊ ቻይና የፀሐይ ግርዶሹ ጎላ ብሎ የሚታይባቸው ስፍራዎች ሲሆኑ በአብዛኛው ኤሲያ ፣ አፍሪካ ፣ ደቡብ እና ምስራቅ አውሮፓ ፣ ሰሜን አውስትራሊያ እንዲሁም የፓስፊክ እና የህንድ ዉቅያኖስ አንዳንድ አካባቢዎች ከፊል የፀሐይ ግርዶሽ እንደሚስተዋልባቸው በናሳ ስለፀሐይ የሚያጠናው የሄሊዮፊዚክስ ሳይንስ ባለሙያ አሌክስ ያንግ መግለጻቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ከዚህ በኋላ በዓለም የፀሐይ ግርዶሽን ለማየት 18 ዓመታትን እንደሚወስድ የዘርፉ ባለሙያ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ደግሞ የአሁኑን አይነት የፀሐይ ግርዶሽ ለማየት ከ140 በላይ ዓመታትን መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
ፀሐይ ግርዶሽ ጨረቃ በፀሐይ እና መሬት መካከል ስትገባ የሚስተዋል ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡
የፀሐይ ግርዶሹን በመሣሪያ ታግዞ ካልሆነ በስተቀር በዓይን በቀጥታ ለማየት መሞከር ጉዳት እንደሚያስከትልም ተገልጿል፡፡