ትራምፕ ቅጣት አልባ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው
ታዋቂዋ 'ፖርን ስታር' ሚስጥር እንዳታወጣ ዝም የማሰኛ ገንዘብ በመክፈል ጥፋተኛ የተባሉት ትራምፕ እስር ወይም ቅጣት የሌለው ፍርድ ተላልፎባቸዋል
ትራምፕ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን እና ውሳኔውን ለማስቀልበስ ይግባኝ እንደሚሉም ዝተዋል
ታዋቂዋ 'ፖርን ስታር' ወይም የወሲብ ሞዴል ስቶርሚ ዳኒኤልስ ሚስጥር እንዳታወጣ ዝም የማሰኛ ገንዘብ በመክፈል በጁሪ ጥፋተኛ የተባሉት ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከእስር ወይም ከቅጣት እንዲያመልጡ ዳኛው በትናንትናው እለት ወስነዋል።
ነገርግን ፍርዱ በታሪክ የሚመዘገብ እና ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን ካደረጉ በኋላ መሰረዝ የማይችሉት ነው ብለዋል ዳኛው።
ዳኛው ጀስቲስ ጁዋን መርቻን በ78 አመቱ ትራምፕ ላይ ያሳለፉት ቅጣል አልባ የጥፋተኝነት ፍርድ ትራምፕ ወደ ኃይትሀውስ ለመግባት ሲያደርጉ በነበረው ጥረት ላይ ጥላ አጥልቶ የነበረውን ጉዳይ ፋይል ዘግተውታል።
ትራምፕ በወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ወደ ኃይት ሀውስ የሚገቡ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ይሆናሉ ተብሏል።
ዳኛው እንደገለጹት በትራምፕ ላይ የእስርም ሆነ የገንዘብ ቅጣት የሌለው ፍርድ ያስተላፉት የአሜሪካ ህገመንግስት ፕሬዝደንቶች በወንጀል እንዳይከሰሱ ስለሚከለክል ነው።
ነገርግን ለፕሬዝደንቶቹ የተሰጠው መብት "የወንጀሉን ክብደት እንማይቀንሰውና መፈጸሙን በምንም መልኩ ምክንያታዊ እንደማያደርግ" ዳኛው ተናግረዋል።
ለፕሬዝደንቶች የተሰጠው የህግ ከለላ መብት ልዩ እና ሌሎችን በሙሉ ሚሽር መሆኑን የገለጹት ዳኛው የጁሪውን ውሳኔ ግን የማጥፋት አይችልም ብለዋል።
ትራምፕ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን እና ውሳኔውን ለማስቀልበስ ይግባኝ እንደሚሉም ዝተዋል።
ከጠበቃቸው ጋር በቴሌቭዥን ስክሪን ላይ የቀረቡት ትራምፕ ጉዳዩ የእሳቸውን የምርጫ ቅስቀሳ ለማደናቀፍ የተቀነባበረ ያልተሳካ ሙከራ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
"ፍጽም ንጹህ ነኝ። ስህተት አልሰራሁም" ብለዋል ትራምፕ።
ትራምፕ ባለፈው አመት ለስድስት ሳምንት በተካሄደው ክስ ቃላቸውን አልሰጡም፤ ነገርግን ጉዳዩ መርቻንን እና የማንሀተን ዲስትሪክት አቃቤ ህግን አልቪን ባራግን በአደባባይ በሚሰጧቸው መግለጫዎች በተደጋጋሚ አንኳሰዋቸዋል።
ጁሪው በትራምፕ ላይ በሙሉ ድምጽ የጥፋተኝነት ብያኔ ማሳለፉን እና ብያኔውም መከበር እንዳለበት የገለጸው አቃቤ ህግ ትራምፕ አቤቱታ ማቅረብ ይችላሉ ብሏል።
ትራምፕ በዓለ ሲመታቸው ትንሽ ሲቀረው በግዛት ዳኞች ፊት ተገደው ላለመቅረብ ከፍተኛ ትግል አድርገው ነበር። ትራምፕ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንዲያስቆም ትናንት በመጨረሻ ሰአት አቤቱታ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ውድቅ ሆኖባቸዋል።
ዳኛው ችሎቱን ሲዘጉ "ጌታው፣ ሁለተኛው የስልጣን ዘመንህ እንዲሳካልህ አመኛለሁ" ብለው ትራምፕ አሰናብቷቸዋል።
ትራምፕ የመንግስት ሰነዶችን በመደበቅ፣ የንግድ ልውውጦችን በማሳሳትና ከእሳቸው ጋር የወሲብ ግንኙነት አለኝ ላለችው ስቶርሚ ዳኒኤልስ 130ሺ ዶላር በመክፈል እና በሌሎች 34 ክሶች ጥፋተኛ የተባሉት ባለፈው ግንቦት 30፣2024 ነበር።
ትራምፕ የቀረቡባቸውን ሁሉንም ክሶች አልፈጸምኩም ሲሉ አስተባብለዋል።