ትራምፕ ከፑቲን ጋር የሚያደርጉት ንግግር እየተመቻቸ መሆኑን ገለጹ
የትራምፕ አማካሪዎች ሰፊ የዩክሬንን ግዛት ለሩሲያ አሳልፎ በመስጠት ስላም ስምምነት እንዲደረስ ሀሳብ አቅርበዋል
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የምትመራው አሜሪካ ለዩክሬን የ 60 ቢሊዮን ሴኩሪቲ ድጋፍ ጨምሮ 175 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን ድጋፍ አድርጋለች
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከፑቲን ጋር የሚያደርጉት ንግግር እየተመቻቸ መሆኑን ገለጹ።
ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድማር ፑቲን ጋር የሚያደርጉት ንግግር እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል። ነገርግን ሪፐብሊካኑ ትራምፕ በሁለቱ መሪዎች መካከል ንግግር የሚካሄድበትን የጊዜ መርሃግብር በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ከሁለት ሳምንት በኋላ የትራምፕ ወደ ኃይትሀውስ መመለስ በየካቲት 2022 ለተጀመረውን የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። ይሁን እንጂ ሊኖር የሚችለው የሰላም ስምሞነት ዩክሬንን ከባድ ዋጋ ሊያስከፍላት ይችላል ተብሏል።
የትራምፕ አማካሪዎች ሰፊ የዩክሬንን ግዛት ለሩሲያ አሳልፎ በመስጠት ስላም ስምምነት እንዲደረስ ሀሳብ አቅርበዋል።
"ፑቲን ማግኘት ይፈልጋል፤ እኛ እያመቻቸን ነው" ሲሉ ትራምፕ በፍሎሪዳ ፓልም ቢች ውስጥ በሚገኘው ማራ-ራ ላ ጎ ከሪፐብሊካን ገዥዎች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ወቅት ተናግረዋል።
ትራምፕ "ፕሬዝደንት ፑቲን ማግኘት ይፈልጋል፣ ይህን በአደባባይ ተናግሯል። እኛ ያ ጦርነት እንዲያበቃ እንፈልጋለን። ያ ከባድ ደም አፋሳሽ ችግር ነው" ብለዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የምትመራው አሜሪካ ለዩክሬን የ 60 ቢሊዮን ሴኩሪቲ ድጋፍ ጨምሮ 175 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን ድጋፍ አድርጋለች። ይሁን እንጂ ጦርነቱን በፍጥነት አስቆማለሁ በሚሉት ትራምፕ አስተዳደር ስር አሜሪካ በእዚያ መጠን እርዳታ ማቅረብ መቀጠሏ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ፑቲን የትራምፕን ለመገናኘት ፍላጎት እንደሚቀበሉ፣ ነገርግን እስካሁን ይፋዊ ጥያቄ አለመቅረቡን በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ትራምፕ ቢሮ እስከሚገቡ ድረስ መጠበቅ አስፈላጊ ይሆናል ብለዋል ፔስኮቭ።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ትራምፕ 34 ወራት ያስቆጠረውን ጦርነት ውጤት በመወሰን እና ፑቲንን በማስቅም ሚና እንደሚኖራቸው እየገለጹ ናቸው።