ትራምፕ በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ሊያነሱ ይችላሉ በሚል የአውሮፓ ሀገራት ስጋት እንዳደረባቸው ተገለጸ
ሞስኮ ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት በባይደን አስተዳደር የተጣሉ ማዕቀቦችን ተመራጩ ፕሬዝዳንት ሊሰርዙ እንደሚችሉ ተነግሯል
ከጦርነቱ መጀመር በኋላ በኢኮኖሚ ፣ በፋይናንስ እንቅስቃሴ ፣ በአለም አቀፈ ገበያ ተሳትፎ እና በሌሎች ዘርፎች አሜሪካ በሩስያ ላይ ማዕቀቦችን ጥላለች
ትራምፕ በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ሊያነሱ ይችላሉ በሚል የአውሮፓ ሀገራት ስጋት እንዳደረባቸው ተገለጸ
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በባይደን አስተደደር በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ሊሰርዙ ይችላሉ በሚል አውሮፓውያን ሀገራት በስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ፋይናንሻል ታይምስ ዘግቧል፡፡
በ2022 የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ሞስኮ 40 ሺህ የሚደርሱ የምዕራባውያን ማዕቀቦችን እያስተናገደች ነው፡፡
በብራስልስ የሚገኘው የአውሮፓ ሀብረት በባይደን የስራ አስፈፃሚ ትዕዛዞች የተተገበሩ ማዕቀቦች የሚሰረዙ ከሆነ በህብረቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉት ማዕቀቦች የትኞቹ እንደሆኑ ለመገምገም ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ፋይናንሻል ታይምስ ያነጋገራቸው የህብረቱ ባለስልጣናት ትራምፕ የባይደንን የውጭ ፖሊሲ ውሳኔዎች ሲገመግሙ የአውሮፓ ህብረት ስትራቴጂያዊ ፍላጎቶችን ሙሉ በሙሉ ችላ ሊሉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ማዕቀቦቹ በባይደን አስተዳደር ስለተጣሉ ብቻ ትራምፕ ሊሰርዟቸው ይችላሉ ብለዋል፡፡
ባይደን የሩሲያን ኢኮኖሚ ወደ ኋላ ይመልሳል ወይም ከጦርነቱ ጋር ተዳምሮ አቅሙን ይቀንሰዋል ያሉትን ተከታታይ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሞስኮ በውጭ ሀገራት ያሏትን ከፍተኛ ንብረቶች እንዳታንቀሳቅስ አስተዳደሩ ከአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች ቀጠናዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን አግዷል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፣ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅቶች ፣ ሩስያዊ ባለሀብቶች ፣ የንግድ ተቋማት እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት የማዕቀቡ ሰለባ ሆነዋል፡፡
ማዕቀቦቹ በዋናነት የሩሲያን የመዋጋት አቅም በመቀነስ ከዩክሬን ተሻግራ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ላይ ጦርነት የምትከፍትበትን እድል ማሳነስ እንዲሁም አጠቃላይ የምጣኔ ሀብታዊ ጉዞዋን ማሰናከል አላማ ያደረጉ ናቸው፡፡
የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት እንዳሉት ትራምፕ የተወሰኑ ማዕቀቦችን የሚያነሱ ከሆነ በሩስያ ሁለንተናዊ አቋም ላይ የቅርጽ ለውጥ የሚያስከትል ይሆናል፡፡
የሚያሸንፉ ከሆነ ጦርነቱን በ24 ሰአት እንደሚያስቆሙ በተደጋጋሚ ሲገልጹ የተደመጡት ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ቅድሚያ ከሚሰጧቸው አጀንዳዎች መካከል የዩክሬን ጦርነትን ማስቆም አንድኛው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡