ቱርክ፤ ስዊድን እና ፊንላንድ የአንካራን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እርምጃ መውሰዳቸውን ገለጸች
አንካራ፤ ሀገራቱ ተጨባጭ እርምጃ ቢወስዱም ጥያቄያቸውን ለማጽደቅ አሁንም በቂ እንዳልሆነ ገልጻለች
ስዊድን፤ የአንካራን ስጋት ለመቅረፍ በዚህ ሳምንት አዲስ የጸረ-ሽብርተኝነት ህግ ለፓርላማ የምታቀርብ ይሆል
ስዊድን እና ፊንላንድ ባለፈው አመት ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ሁለቱ ሀገራት በአንካራ እና በምዕራባውያን አሸባሪ ተብለው የሚፈረጁትን የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ አባላትን ያግዛሉ በሚል በቱርክ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞዋቸው ወደ ጥምረቱ ሳይቀላቀሉ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ላለፉት በርካታ ጊዜያት ስዊድን እና ፊንላንድን ወደ ኔቶ የመቀላቀል ጥያቄን ስትቃወም የቆየችው ቱረክ አሁን ላይ ሀገራቱ ወደ ጥምረቱ እንዲቀላቀሉ ልትፈቅድ እንደምትችል የስዊድን ዋና ተደራዳሪ ገልጸዋል፡፡
በአንካራ በኩል እንደቅድመ ሁኔታ ሲቀርብ የነበረ ጉዳይ ለማሟላት በስዊድን እና ፊንላንድ የተወሰዱ ተጨባጭ እርምጃዎችን በቱርክ በኩል እውቅና ማግኘታቸውንም ነው የተናገሩት ዋና ተደራዳሪው ኦስካር ስቴንስትሮም ፡፡
ኦስካር ስቴንስትሮም በኔቶ ዋና መስሪ ቤት በሰጡት መግለጫ "ቱርክ በዚህ ስምምነት ላይ ሁለቱም ስዊድን እና ፊንላንድ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን መገንዘቧን አይተናል፤ ይህ ጥሩ ምልክት ነው”ም ብለዋል፡፡ ጊዜው በግልጽ ባይናገሩም ሀገራቱ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ የሶስትዮሽ ድርድር ለማድረግ መስማማተቸውንም ጭምር በመግለጽ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ቃል አቀባይ ኢብራሂም ካሊን፤ ስዊድን እና ፊንላንድ የአንካራን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የወሰዱት እርምጃ አዎንታዊ ቢሆንም የኔቶ አባልነት ጥያቄያቸውን ለማጽደቅ ለቱርክ አሁንም በቂ አይደለም ብለዋል።
" በነበረውድረድር የቱርክን የደህንነት ስጋቶች እና ከሀገራቱ የሚጠበቁትን ነገሮች በድጋሚ አጉልተናል" ያሉት ቃል አቀባዩ "የጉዳዩ አካሄድና ፍጥነት የሚወሰነው ሀገራቱ በሚወስዱት እርምጃ ይሆናል " ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሀገራቱ ለጉዳዩ መፍትሄ ለማበጀት የሚስችሉ የሶስትዮሽ ድረድር ለማድረግ ባለፈው አመት በማድሪድ ከስምምነት መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ በቅርቡ በስዊድን በሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ ቅራቢያ በተደረገ ተቃውሞ አንድ የቀኝ አክራሪ ፖለቲከኛ የሙስሊሞችን ቅዱስ ቁርዓን መጽሐፍ ማቃጠሉን ተከትሎ ቱርክ ከሶስትዮሽ ድርድር ራሷን አግልላ እንደነበር ይነገራል፡፡
አንካራ ግን በተለይ ስዊድን የማድሪድ ስምምነትን በከፊል መተግበር እንዳልቻለች በተደጋጋሚ ስተወቅስ ትደመጣለች፡፡
አንካራ ይህን ትበል እንጅ ስቶክሆልም በሶስትዮሽ ድርድሩ የተነሱ ግዴታዎቿን እየተወጣች መሆኗን ዋና ተደራዳሪው ስቴንስትሮም ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት የአንካራን ስጋት ለመቅረፍ በዚህ ሳምንት አዲስ የጸረ-ሽብርተኝነት ህግ ለፓርላማ ያቀርባልም ብለዋል።