ቱርክ በፈራረሱ ህንጻዎች ዙሪያ ከ600 በላይ ሰዎች ላይ ምርመራ ጀምራለች
እስካሁንም 184 የህንጻ ተቋራጮች እና ባለቤቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል
በቱርክና ሶሪያ ከሶስት ሳምንት በፊት በደረሰው የርዕደ መሬት አደጋ የሟቾች ቁጥር 50 ሺህ ደርሷል
በቱርክ ከደረሰው አሰቃቂ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ጋር በተያይዘ ከ600 በላይ ሰዎች ምርምራ እየተደረገባቸው መሆኑን የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስትሩ በኪር ቦዝዳግ ዛሬ ይፋ እንዳደረጉት እስካሁን 184 የህንጻ ግንባታ ተቋራጮች እና የህንጻ ባለቤቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ለርዕደ መሬት አደጋ ተጋላጭነቷ ከፍ ያለው ቱርክ፥ የሚገነቡ ህንጻዎች አደጋ የሚቋቋሙ እንዲሆኑ ጠንካራ የህንጻ ግንባታ ህግ ብታወጣም አፈጸጸሙ ዝቅ ያለ መሆኑን ከሶስት ሳምንት በፊት የተከሰተው አደጋ አሳይቷል።
በርዕደ መሬቱ ከ160 ሺህ በላይ ህንጻዎች መፈራረሳቸውንም ነው የቲ አር ቲ ዘገባ የሚያሳየው።
አንካራ ለደረሰው ውድመት የህንጻ ግንባታ ህጉ አለመፈጸምን በመጥቀስ ከሁለት ሳምንት በፊት 113 የህንጻ ተቋራጮችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የእስር ማዘዣ ማውጣቷ ይታወሳል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥም ርዕደ መሬቱ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰባት ከተማ ከንቲባ ይገኙበታል።
በአሁኑ ወቅትም ከ600 በላይ ሰዎች ከፈራረሱት ህንጻዎች ጋር በተገናኘ ምርምራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ነው የፍትህ ሚኒስትሩ በኪር ቦዝዳግ የተናገሩት።
ሚኒስትሩ ይህን መረጃ በቴሌቪዥን ይፋ ሲያደርጉ በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 ሆኖ የተመዘገበ አዲስ ርዕደ መሬት መከሰቱ ተገልጿል።
አደጋው ያደረሰው ጉዳት ግን እስካሁን አልተገለጸም።
ቱርክን ደጋግሞ እየጎበኛት ካለው የርዕደ መሬት አደጋ ጋር በተያያዘ መካሰሱም ቀጥሏል።
የሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አስተዳደር የህንጻ ተቋራጮችን ተጠያቂ አድርጎ በርካቶችን በቁጥጥር ስር ሲያውል፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ ህጉን ማስፈጸም ያልቻለው ራሱ የኤርዶሃን አስተዳደር ነው በሚል ይሞግታሉ።
የግንባታ ዘርፉን ለማበረታታት ሲባል ለርዕደ መሬት አደጋ ክፉኛ ተጠቂ በሆኑ አካባቢዎች ጭምር የህንጻ ግንባታ ህጉን የጣሰ ግንባታ ላካሄዱ ተቋራጮች የሚደረገውን ምህረት በማንሳት።
በ10 ከተሞች ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ከደረጃ በታች ለሆኑ ህንጻዎች የተደረገው ምህረትም አደጋው አሰቃቂ እንዲሆን ስለማድረጉ አብራርተዋል።
ለ20 አመት ስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን፥ ሀገሪቱን ለሚያሰጋት ርዕደ መሬት ምንም አይነት ዝግጅት አላደረጉም የሚል ወቀሳም ከተቃዋሚዎች ጎራ መነሳቱ ቀጥሏል።
በሰኔ ወር 2023 ፕሬዳንታዊ ምርጫ የሚያደርጉት ኤርዶሃን ግን “ክፉ እጣፈንታ” ያሉትን አደጋ ማስቀረት እንደማይቻል ነው የተናገሩት።
በቱርክና ሶሪያ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው አደጋ ሌሎች ሀገራትም ርዕደ መሬትን የሚቋቋም ህንጻ ግንባታ ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስጠነቅቅ ነው ተብሏል።