ኢኮኖሚ
ትዊተር የአፍሪካ ዋና መቀመጫውን በጋና ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ጽህፈት ቤት በጋና በመሆኑ ነው ትዊተር አክራን ለአፍሪካ ቢሮው የመረጠው
የጋና ፕሬዘዳንት በትዊተር ውሳኔ መደሰታቸውን እና መንግስታቸው ለድርጅቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል
በአሜሪካዊው ጃክ ዶርሴይ የሚመራው ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ትዊተር ፣ ዋና መቀመጫውን ሳንፍራንሲስኮ በማድረግ ወደ ሁሉም የዓለማችን አገራት ይደርሳል።
በ19 አገራት ቢሮ ያለው ይህ የትስስር ገጽ የአፍሪካ ቢሮውን በምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና መዲና አክራ እነደሚያደርግ በትዊተር ገጹ ይፋ አድርጓል።
የጋና ፕሬዘዳንት ናና አኩፎ በትዊተር ውሳኔ መደሰታቸውን እና መንግስታቸው ለድርጅቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ትዊተር የአፍሪካ ቢሮውን በናይጄሪያ ፣ በኬንያ ወይም በደቡብ አፍሪካ ሊከፍት እንደሚችል ግምታቸውን ቢያስቀምጡም ኩባንያው ጋናን መርጧል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ጽህፈት ቤቱን በጋና እንዲሆን መወሰኑ ፣ ትዊተር አክራ ከተማን ለአፍሪካ ቢሮው እንድትሆን ለመምረጡ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።
በፈረንጆቹ በ2006 ዓመት ቢዝ ስቶን ፣ ጃክ ዶርሴይ እና ኖህ ግላስ በተባሉ ሶሰት ወጣቶች የተመሰረተው ትዊተር ከ350 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አሉት።